Tuesday, November 13, 2012

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ ዛሬ ፍ/ቤት ቀረቡ

ኢሳት ዜና:-በእነ አንዷለም ዓራጌ መዝገብ በተከሰሱት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ንብረት እንዲወረስ ዓቃቤ ሕግ በጠየቀው መሠረት ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ በዛሬው እለት ፍ/ቤት መቅረባቸው ታውቋል።

በንብረቱ የዕግድ ትዕዛዝ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ የተጠየቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መንግስት ይውሰደው አልከራከርም ባለቤቴም ድርሻዋን እትጠይቅም በማለት ልፍርድ ቤቱ ምላሽ መስጠቱን ከአዲስ አበባ የመጣው ዜና ያስረዳል። ፍ/ቤቱም ሥለራስህ እንጂ ባለቤትህን ወክለህ መናገር አትችልም በማለት ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሠርክዓለም ፋሲል ራስዋ ቀርባ እንድታስረዳ አዟል በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሕዳር 28/2005 ቀጠሮ ሠጥቶ ችሎቱ መነሳቱም ታውቋል።

ዓቃቤ ሕግ እንዲወረስ የጠየቀው የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ቤት ባለ ሁለት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት እንዲሁም የወላጅ እናቱ ቤትና መኪና መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም ወጣቱ ፖለቲከኛና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አንዷለም አራጌ የአንድነት ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ናትናኤል መኮንን እንዲሁም የመኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ክንፈሚካኤል ደበበ በአሸባሪነት ተከሰው ከታሰሩ አንድ አመት ያለፋቸው ሲሆን እስከ እድሜ ልክ የደረሰ ቅጣት እንደተወሰነባቸውም ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment