Saturday, January 18, 2014

የወያኔን የሚዲያ አፈና ማመከን የጊዜው አጣዳፊ ተግባር ነው

January 18, 2014

Ginbot 7 press release in Amharic(ግንቦት 7) ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባችን ስለራሱና ሰለአገሩ ምንም አይነት መረጃ ከአማራጭ የመገናኛ ብዙሃን ምንጮች እንዳያገኝ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ድርግም አድርጎ ዘግቶ ኖሮአል።
የወያኔ መሪዎችና ተሿሚዎች በየግላቸው ምንም ቁብ በማይሰጡትና ተቃዋሚዎች እንዲያከብሩት ነጋ ጠባ በሚወተውቱት የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀጽ 29 ዕውቅና ካገኙ የዜግች መብቶች አንዱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ ሳለ እየተካሄደ ያለውን የሥልጣን ብልግናና አገሪቱን እያራቆተ ያለውን ዘረፋ በመተቸታቸው ብቻ በአንድ ወቅት እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የነጻ ጋዜጣ አዘጋጆችና አሳታሚዎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ከፊሉ ከአገር እንዲሸሽ ሌላው አፉን ዘግቶ እንዲቀመጥ አለያም የፈጠራ ክስ እየተመሰረተባቸው እስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል። አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው። በወያኔ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አፈና የአሜሪካና የጀርመን መንግሥታት በየግላቸው የሚያስተዳድሩዋቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮኖች እንኳ ከጥቃቱ ማምለጥ ስላልቻሉ እነሆ እስከዛሬ ያልተቋረጠ የማጥላላት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል።
ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ከቻሉና ከየትኛውም መዲያ መረጃ የማግኘት መብታቸው ከተረጋገጠ ሥልጣን ላይ ውሎ እንደማያድር ጠንቅቆ የተረዳው የወያኔ አገዛዝ በዚህ የሚዲያ አፈና ተግባሩ በመቀጠል ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮን እንዲሁም ህዝብ አልፎ አልፎ ሃሳቡን ለመግለጽ በሚገለገልባቸው ጥቂት የአገር ውስጥ ህትመቶች ላይ የተለመደውን የጥቃት ጅራፉን ለማሳረፍ ታጥቆ ተነስቶአል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በመረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ የህወሃት ቀድሞ ታጋዳላዮች በሚቆጣጠሩትና እንደግል ንብረታቸው በሚፈነጩባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከአሁን ቦኋላ ማንኛዉም የመንግስት ባለስልጣን፤ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ምንም አይነት ቃለመጠይቅ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ እንዳይሰጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል። ማስጠንቀቂያውን ተላልፎ በተገኘ ማንም ሰው ወይም ድርጅት ላይ የአሸባሪነት ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትበትም ዛቻና ማስፈራሪያ በተለመደው የቃላት ጋጋታ ተገልጾአል።
ይህ ከሰሞኑ የወያኔ ብሄራዊ መረጃ ደህንነትና ኮሚኒኬሽን መስሪያቤት ያወጣዉ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዜጎች የሚናገሩትን ፤ የሚጽፉትን፤ የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ብቻ ሳይሆን የሚያስቡትንና ሊደግፉት ወይም ሊቃወሙት ይችላል ተብሎ የሚጠረጠረውን ሁሉ አስቀድሞ ለመቆጣጠር ፍላጎቱ ያለው መሆኑን ነው።