Sunday, August 3, 2014

ሠራዊቱ የህዝብ ወገንተኛነቱን የሚያስመሰክርበት ግዜ እየመጣ ነው

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቀደመው ትውልድ ከቱርክ ኤምፓየር፤ ከግብፅ እና ከደረቡሽ፤ ከጣሊያን ወራሪ፤ ከሶማሊያ ተስፋፊ ኃይል እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተዋግቶ አገሪቷን ለአሁኑ ትውልድ ለማቆየት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። በተለይ ነፍጥ አንግቦ የተሠለፈው ኃይል የከፈለው የህይወት መሥዋዕትነት የሚረሳ አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ለዛሬው ትውልድ የቆየችው ከራሱ ይልቅ ለአገርና ለወገን የሚያስብ ትውልድ በመኖሩ መሆኑ የሚያከራክረን
ጉዳይ አይሆንም።

የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአገር ደህንነት ኃይል የቆመው አገርን ከጥቃት ለመከላከል ነው። አገር በጠላት እጅ ወድቃ በወገን ላይ ስቃይ እንዳይደርስ፤ ህዝቡም አገር አልባ እንዳይሆን መጠበቅ የአገሪቷ የሠራዊትና የደህንነት ኃይል ዋና ተግባር ነበር። ህወሃት መራሹ መንግስት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥም የቆመው ሠራዊት እና የደህንነት ኃይል ተግባሩ ሌላ ሁኗል።
በዚህ ዘመን ሠራዊቱና የደህንነት ኃይሉ የአገርን ብሄራዊ ደህንነት የሚጠብቅ ሳይሆን ህወሃት የተባለውን ዘረኛና ዘራፊውን ቡድን የሚጠብቅ ኃይል መሆንን እንዲመርጥ ሁኖ አገርን ከጠላት የመከላከል ተግባሩን ረስቷል። ይህን ኃይል የሚመሩትም ደማቸውንና አጥንታቸውን ቆጥረው ከአንድ መንደር/ጎሣ የተሰባሰቡ እና ካርታ ይዘው የቆሙበትን ሥፍራ እንኳን ለመለየት የማይችሉ መሃይማን መሆናቸው አገሪቷ ያለችበትን አደጋ ከሚያመላክቱ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው። ህወሃቶች የደርግ ሠራዊት እያሉ ሊሳለቁበት የሚሞክሩት የቀድሞው የአገሪቷ መከላከያ ኃይል ሲመራ የነበረው አውሮፓና አሜሪካን ድረስ ተጉዘው በተማሩ፤ ማዕረጋቸውም የዓለም ዓቀፉን ደረጃ የጠበቀ፤ አገሪቷን ወክለው አደባባይ ቢወጡ የሚያኮሩ እንደነበረ የታወቀ ነው። የሹመታቸው መሠረትም ደምና አጥንት ሳይሆን እውቀታቸው፤ ችሎታቸውና ወታዳራዊ ብቃታቸው ነበረ።በህወሃት የሚመራውን ሠራዊትና የደህንነት ኃይል የሚመሩት ቡድኖች ከቀድሞዎቹ ሥርዓት የጦር መሪዎች ጋር ሲወዳደሩ የጫማቸውን ጠፍር እንኳ ለመፍታት የሚታጩ አይሆኑም።ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንደሚባለው ሆነና ጨካኞችና ነፍሰ ገዳዮች በወንበሩ ቁጭ ብለው የአገሪቷን ውድቀት እያፋጠኑት ይገኛሉ።