Saturday, February 1, 2014

ወያኔን ያሸበረው የግንቦት 7 መንገድ ምንድነው?

የትግራይን ሕዝብ ከብሄር ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በሚል ጠባብ ዓላማ ተደራጅቶና ታጥቆ ለበትረ ሥልጣን የበቃው ህወሃት ወይም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ 23 አመት ሊሞላው እነሆ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተውታል።
ለጋራ ቤታችን ለሆነቺው አገራችን ኢትዮጵያና በአስተዳደር በደል ለከፋ ድህነት ለተዳረገው መላው ሕዝቦቿ የሚሆን አንዳችም ራዕይ ሳይኖረው ለመንግሥትነት ሥልጣን የበቃው ይህ ቡድን ላለፉት 23 ዓመታት ከግል ኑሮአቸው አሻግረው የአገርንና የወገንን ጥቅም ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉትን በዙሪያው አሰባስቦ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ የሃብት ምዝበራ ወንጀል በተጨማሪ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና አፈና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ሰሞኑን እያፈተለኩ በመውጣት ላይ ከሚገኙ ምስጥራዊ የድምጽ መረጃዎች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ደግሞ ለጥቂቶች የሃብትና የብልጽግና ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በአንድ በኩል በምርጫ ስም እንዴት አድርገው ሕዝቡን ቀፍድደው የምርጫው ተሳታፊ ማድረግ እንደሚችሉ ሲዶልቱና በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የሌሉትንና ለሥልጣናቸው ያሰጉናል ያሉዋቸውን የደሃዉን ልጅ በማጋፈጥ እንዴት በጦርነት እንደሚጨፈልቁዋቸው ሲመክሩ ተሰምተዋል።
ከወያኔው ቁንጮ አንዱ የሆነው በረከት ስሞን በየደረጃው ላሉት የአገዛዙ ሹሞችና ካድሬዎች ባደረገው ገለፃ መሬትን የመንግሥት ባደረገው ኮሚኒስታዊ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ጭሰኛ ለመሆን የተፈረደበትን ሰፊውን አርሶ አደር “ተኛ ስንለው ይተኛል፤ ቁም ስንለው ይቆማል ፤ እንደፈለግን ብንበድለው እንኳ አያማርረንም ” እያለ ሲዘባበትበት ተደምጦአል ። በአንድ ለአምስት ኮሚንስታዊ አደረጃጀት ተጠርንፎ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብቻ የሚያቀርቡትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለውዴታው እንዲራገፍበትና ከአቅሙ በላይ ዕዳ እንዲቀፈቅፍ የተፈረደበት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዚህ አይነት ንቀት ደረጃ የሚዘባበትበትን መሪ ከወያኔው በረከት ስሞን በፊት ገጥሞት አያውቅም ። ለወደፊትም ሊያይ አይፈልግም ። ወያኔን ሥልጣን ላይ ለማምጣት የሰሜኑ ክፍለአገራችን አርሶ አደር የተጫወተው ሚና ተዘንግቶ በበረከት ስሞን እንዲህ መዋረዱ እጅግ ያሳዝናል። ለነገሩ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለድል ያበቃው የትግራይ ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያየ አይደል?
ሌላው አስገራሚ ክስተት በአገር ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ባደረጉት ዝግ ስብሰባ ታማኝነታችን ለአገራችን ነው ወይስ የሥርዓቱን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም? ብለው ላነሱት ጥያቄ የጠቅላይ ሚንስትር ተብዬው የህግ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሰጠው መልስ ነው። ደህንነት ብቻ ሳይሆን የመከላኪያ ሠራዊትና ፖሊስ ጭማር ታማኝነታቸውና ግዴታቸው ሥርዓቱን ሥልጣን ላይ ማቆየት መሆን አለበት ሲል ጌታቸው እንቅቹን ነግሮአቸዋል ። በምላሹ “ላለፉት 23 አመታት እያደረግነው ያለው ይሄው ሆኖ ሳለ አሁን ምን ብታስቡ ነው ጥያቄ ያነሳችሁ?” የሚል ይመስላል ። ይባስ ብሎም ሥርአቱን ለመጠበቅ ያልቻለና በግንቦት 7 መንገድ የሚጓዝ ደህንነት ሠራተኛ የተስፋየ ገብረስላሴን ያህል የደህንነት እውቀት ቢኖረውም ሆነ እስራኤል አገር የዓመታት ስልጠና ያገኘ ቢሆን ዋጋ የለውም ብሏቸዋል።
ለመሆኑ ወያኔዎች እንደመርገም የቆጠሩትና ተከታዮቻቸውን የሚያስፈራሩበት የግንቦት 7 መንገድ ምንድ ነው።?