Tuesday, September 3, 2013

በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተወሰደውን ህገ-ወጥ ርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን!!! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ (አንድት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የተወሰደበትን ሕገ-ወጥ ርምጃ አጥብቀን የምንቃወም ሲሆን፤ ይህንን የፈፀሙ አካላትም በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡
እንደሚታወቀው ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድ ወር አስቀድሞ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን እንዳሳወቀ የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ ቀንም የሀይማኖቶች ጉባኤ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱ መገለፁ አደናጋሪ ነበር፡፡ ይህንን የሁለት አካላትየሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ በሰከነ መንገድ የአዲስ አበባ መስተዳድር መፍታት ሲገባው ችግሩ እንዲከር አድርጓል፡፡ ይህም የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን የመዝጋትና የማናለብኝነት አንዱ መገለጫ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቅዳሜ ምሽት በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሰላማዊ ትግሉ ላይ እየተፈፀመ ያለ ርምጃ ነው፡፡ የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱት የማገት፣ የማፈንና የመደብደብ ርምጃ አሳፋሪ ሆኖአግኝተነዋል፡፡ ፀጥታ አስከብራለሁ የሚለው የፖሊስ አካል መብትን በድብደባ ለማስቆም የሄደበት መንገድም ህገ-ወጥ ነው፡፡ ስለዚህ ፓርቲያችን አንድነት መንግስት እያካሄደ ያለውን የአፈናና የጉልበት ርምጃ አቁሞ አሁንም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ህገወጥነትን መቃወሙን አጠናክሮ በመቀጠል የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ ትግል እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አባባ