መግቢያ
የዳውሮ ሕዝብ የደረሰበትን የመልካም አስተዳደር እጦት፤ በአቅራቢያው ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት አለመቻል፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሕዝቡ ለሚያቀርበው የመብት
የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ያለመስጠት፤ በየወቅቱ በሚፈራረቁ የሥልጣን ተረኛ በሆኑት የህወሐት/ ደኢህዴን ካድሬዎች የግል ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ የወረዳ ማዕከል እየተወሰነ ከመንደር ወደ መንደር በመዘዋወሩ የተነሳ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት አለመቻል አበሳጭቶት ወደ አምጽ ማምራቱን በመዘርዘር ከዚህ በፊት በሦስት ክፍሎች ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ ማስነበቤ ይታወሳል።
አሁንም በሕወሃት/ ደህዴን ካድሬዎች ተንኳሽነት የተነሳ የሕዝቡ ቁጣ እንደገና እያገረሸ መጥቷል። እስሩ ማንገላታቱ ከሥራ ማባረሩ ተጀምሯል። የሕዝቡ ጥያቄ የሚታወቅና ግልጽ ነው። ከሚዲያና ከካድሬዎች የሚነገረውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ የልማትና እድገት ፕሮፓጋንዳ ባሻገር ድርሻውን ማግኘት ቀርቶ በአይኑ ለማየት አለመቻል፤ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማግኘት ያለመቻላቸውና የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየናረ መምጣት፤ አንድ አርሶ አደር ወደ ወረዳ ማዕከል ለመድረስ ከአንድ ቀን በላይ ለሚፈጅ ጊዜ በእግሩ መጓዝ የግድ እየሆነበት ስለመጣና ይህም ስላሰለቸው፤ ያላግባብ እንዲርቀው የተደረገው የወረዳ ማዕከል በሚፈልገውና ወደ ሚቀርበው ሥፍራ እንዲዛወርለት ያቀረበው ተደጋጋሚ አቤቱታ ሰሚ ሊያገኝ አለመቻሉ፤ ጥያቄውን ለመንግሥት በየደረጃው በተደጋጋሚ አቅርቦ መፍትሄ አለማግኘቱ ሕዝቡን በጣም አሳዝታል። በዚህም የተነሳ የዳውሮ ዋካን ሕዝብ ጥያቄ ያነገበው ጀግናው ሰማዕት መምህር የኔሰው ገብሬ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና የመልካም አስተዳደር እጦት በመቃወምና ድርጊቱን በማውገዝ ራሱን በእሳት በማቃጠል መስዋዕትነት መክፈሉ ይታወቃል። ይህም ሆኖ የዳውሮ ሕዝብ በደል መፍትሄ እስካሁን ሊያገግኝ አልቻለም።
የተቃውሞው እንደገና መቀስቀስ ምክንያት
ህወሐት/ ደኢህዴን በደቡብ ክልል በአንዳንድ ዞኖች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሳበትን የህዝብ ተቃውሞ መቀነስ ስለሚችልበት ሁኔታ ተወያይቶ ነበር። በዚህ ውይይት ላይ በዋናነት የተነሳውና የታመነበት ነጥብ የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄና የወረዳ ማዕከል ጉዳይ ሆኖ በውይይቱ ጎልቶ ወጣ። በመቀጠልም እንዴት አድርገው የህዝቡን ቁጣ ማርገብ እንደሚቻልና ምንም ተጨማሪ ወረዳ ሳይሰጥ ሕዝቡን የማሳመን ሥራ መሥራት እንደሚገባ ታምኖበት ለአፈጻጸም ለሚመለከተው የፖለቲካ ኃላፊዎች እንዲያስፈጽሙት ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ሕዝቡ እንዲወርዱ ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ በአንክሮ የተነሳው የቀድሞው ሰሜን ኦሞ ዞን ሥር የነበሩት ዞኖች መካከል የጋሞጎፋና የዳውሮ ዞኖች ህዝብ ጉዳይ ነበር። በዚህ መነሻነት የዞን አመራሮች ሕዝባቸውን የማሳመን ሥራ እንዲሰሩ የሚያስገድድ መመሪያ ለዞኑ የፖለቲካ አመራርች ይወርዳል። አመራሮቸ እንዲያስፈጽሙ ታዘዙ። በዚህ መነሻነት ነው እንግዲህ በእስርና በእንግልቱ ሳቢያ ዝም ያለና ጊዜ የሚጠብቅ፤ ግን ውስጥ ውስጡን እየፋመና እየጋመ የነበረን የህዝብ ብሶት እንደገና ቀሰቀሱት።
የዳውሮ ህዝብ ያቀረበው የፍትና የመብት ጥያቄ በመሆኑ ከዛሬ ነገ ይመለስልኛል ብሎ በሚጠበቅበት ወቅት መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጥያቄውን ለማድበስበስና ከሕዝቡ የተሻለ ለሕዝቡ አሳቢ በመምሰል ወረዳ ምን ያደርግላችኋል? ልማት ነው የሚያስፈልጋችሁ! ከልማትና ከወረዳ ምረጡ! ተጨማሪ ወረዳ አይጠቅማችሁም! የወረዳ ርእሰ ከተማ ቢርቅባችሁም ራቀብን አትበሉ! ዝም በሉ! እንዲያውም ፍትህ ፍለጋ ስንቅ ተሸክማችሁ በእግራችሁ ረጅም ሰዓት በመጓዛችሁደስ ደስ ሊላችሁ ይገባል! የሚል ስሜት ያዘላ አድራቂ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ለማወናበድ እየተሞከረ ይገኛል። የመንግሥት ሠራተኛው የህዝብ ልጅ እንዳልሆነና የሕዝብ በደልን የማይረዳ በማስመሰል ከሕዝቡ ሓሳብ በተቃራኒው ከአመራሮች ጎን እንዲቆም ለማድረግ በየወረዳው ካድሬ ተመድቦ ተግቶ እንዲሰራ ይደረጋል።
ካድሬዎች በሕዝቡ መካከል እጅግ የሚገርምና ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ጀመሩ። የማረቃ ዋካ ወረዳ ዋና ከተማ ዋካ ይሁንልን የሚልን የህዝብ ጥያቄ ለማፈን የማይቻል መሆኑ ግልጽ ነው። በማሰር በማፈን በሐሰት በመክሰስና በመወንጀል በማስፈራራት ጥያቄውን ምላሽ እንዳያገኝ ማድረግ አምና ተችሏል። ይህ ማለት ግን ሕዝቡ ጥያቄውን ትቶታል ወይም መልስ አግኝቷል ማለት አይደለም። የወረዳው ማዕከል አያማክለንም የሚለውን የሕዝብ ጥያቄ ለማፈንና ምላሽ ላለመስጠት ሲባል ለዘመናት አብሮ የኖረንና ቤተሰብ የሆነውን የማሪና አካባቢውን ሕዝብ በመቀስቀስና በዋካ ከተማ ሕዝብ ላይ ለማነሳሳት መቀስቀስ ቀጠሉ።
የማረቃ ወረዳ ሕዝብ ከቆዳ ስፋቱና ከሕዝብ ቁጥር አንጻር እንዲሁም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ የተነሳ ሁለት ወረዳ ሊሆን ይገባል የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት ያለው ነው። በዚህ የተነሳ ዋካና ማሪ ሁለት የተለያዩ ወረዳዎች መሆን ይገባቸዋል የሚል ሐሳብ ይዞ መነሳት ነው የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ ማለት። ነገር ግን ቀድሞ የነበረን ወረዳ የወረዳው ማዕከል ይርቀናል አያማክለንም የሚልን ጥያቄ ለማፈን ሌላ ተገቢ ያልሆነ ቅስቀሳ ሕዝብ ውስጥ መርጨት ተጀመረ።
በምንም ዓይነት ሁኔታየኢትዮጵያ ዋና ከተማ ኬንያ ጠረፍ የሚገኝ ቀበሌ ሊሆን አይችልም። የትግራይ ክልል ዋና ከተማ ደሴ አልተደረገም። ዳውሮ ውስጥ ብትመለከቱ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። የሎማዲሳ ወረዳ ዋና ከተማ ገሳ ጨሬ ይባላል። ይህ አዲስ የተቆረቆረ ከተማ ያለው በአጎራባቹ የጌና ቦሳ ወረዳ ውስጥ ነው። የሎማ ዲሳ ወረዳ ሕዝብ የጠየቀው የወረዳችን ዋና ከተማ ከአጎራባች ወረዳ ወጥቶ ቢያንስ እንደቀድሞው ወደ ወረዳችን መሐል አካባቢ ተመልሶ በሚያማክለን ሥፍራ ይደረግልን ነው። ይህንን ጥያቄ አይቶና ሰምቶ መፍትሔ የሚሰጥ አመራር የለም።
በመንግሥት ውሳኔ የተጣመሩ ወረዳዎች ዳግም በመንግሥት ውሳኔ ተለያይተው ቀድሞ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሲደረግ የወረዳው ማዕከል ጉዳይ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ውይይት ተደርጎበት ሊወሰን ሲገባ ይህ ሳይሆን ቀርቷል። ታዲያ ይሄ ስህተት የማነው? የሕዝቡ ነው ወይስ የአመራሩ ነው? ከዲሳ አካባቢ ለምሳሌ ቃኢ ጌሬራና ከዚያ ርቆ የሚኖር አንድ አርሶ አደር የወረዳውን አስተዳደር ፍለጋ አንድ ቀንና ከዚያ በላይ መጓዝ አለበት የሚል የወረዳና የዞን አመራር እውነት ለህዝቡ የቆመ ነው? አመራሩ ለምንድነው የሚመራውን ሕዝብ የማይሰማው? እውነት አሁን የዲሳ አካባቢ ህዝብ ወደ ገሳጨሬ እንዲመላለስ ተገቢ አይደለም ያለ የመንግሥት ሠራተኛ ሊዋከብ ሊታሰርና ከሥራ ሊታገድ ተገቢ ነው?
የዳውሮ ህዝብ የወረዳ ማዕከል ለአቤቱታ ሲሄድ እንደ ዘመነ ምንሊክ ከቤቱ ስንቅ ቋጥሮ በእግሩ ከአንድ ቀን በላይ በመጓዝ ላይ ይገኛል። በሎማ ወረዳ ዲሳ አካባቢ አገልግሎት ማለት ጋሞ ጎፋ ዞን አዋሳኝ አካባቢየሚገኝ ቀበሌ ማለት ነው። ከዚያ ተነስቶ አንድ አርሶ አደር የወረዳው ማዕከል ወደተሰደደበት ሌላ ወረዳ ማለትም ጌና ቦሳ ወረዳ ከአንድ ቀን በላይ መጓዝ ግድ ይለዋል። ከዚያ በኋላ ተጨማሪ የመኪና ጉዞ አድርጎ ነው ገሳ ጨሬ የሚደርሰው። ይህ ነው እንግዲህ እውነቱ። ልዩነቱ ጥቂት የእግር ጉዞ ሰዓታት ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ችግሩ በቶጫም ሆነ በማረቃ ወረዳዎች ተመሳሳይ ነው።
የሎማን ወረዳ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ የቶጫ ወረዳም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ተርጫ አጠገብ ዋራ አካባቢ የሚኖርን አንድ አርሶ አደር ከጪ ድረስ ተጉዞ ፍትህ እንዲያገኝ ማስገደድ ምን ይባላል? ከጪ ኢሰራ ወረዳ አጠገብ ነው። ቀደም ሲል ኢሰራና ቶጫ ወረዳዎች እንዲጣመሩ በተደረገ ጊዜ ሁለቱን ወረዳዎች እንዲያማክል በሚል የተመሰረተ ከተማ ነው። ወረዳዎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሲወሰን የኢሰራ ወረዳ ከተማ ወደ ቀድሞው ማዕከል ሲመለስ ቶጫ ወረዳ ግን ቀደም ሲል ወደ ነበረበት ሥፍራ ሳይመለስ እዚያው እንዲቀጥል ተደረገ።
ይህ የሕዝብ ጥያቄ ሕብረተሰቡን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ያስተባበረና እያጠናከረው የመጣ ሲሆን በገዢው ፓርቲ ላይ ያለው ጥላቻ እያደገና እየከረረ መጥቷል። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት ካድሬዎች ናቸው። ጀግናው የነጻነት ታጋይና ሰማዕት የሆነው መምህር የኔሰው ገብሬም “ የወረዳና የልማት ጥያቄ በማቅረቡ ወህኒ ቤት ሲያስሩት ጤነኛ የነበረ፤ ሲፈቱት ያልታመመና በሳምንቱ ራሱን በብሶት በቤንዚን አቃጠለ። በተቃጠለ በሦስተኛው ቀን ሞተና ከሞተ በኋላ ደግሞ ፖለቲከኞቹ እንዲሉት ታዘውና ተገደው እብድ ነበር አሉት። የከፈለው መስዋዕትነት የዚሁ ትግል አካል ነበር። ሌሎችም ለሚዲያ ያልበቁ በየወረዳው ፍትህና መልካም አስተዳደር እጦት ለችግራቸው መፍትሄ የሚሰጥ አካል አጥተው በተለያየ መንገድ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። ጊዜና ወቅት ሲፈቅድ የሚታወሱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
እኛ አመራሮቹ የምንፈልገውን አስተጋቡልንም? የወረዳ ጥያቄ ለህዝቡ አይጠቅምም እያላችሁ ሕዝቡን ቀስቅሱልን! የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን ከገዢው ፓርቲ ጋር ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ መተባበር ግዴታው ነው! ይህን ካላደረግህ ጥገኛ ነህ! በሌላ አባባል ህዝቡን ለማፈን መብቱን ለመንፈግ ተነስተናልና የመንግሥት ሠራተኛውም ከእኛ ይተባበር የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ወስነው ለመንግሥት ሰራተኛው ጥሪ አደረጉ። ለዚህ ያልተባበረውን የመንግሥት ሠራተኛ ከሥራ በማገድ በማባረር በማሰር ወዘተ ለማስገደድና አንገቱን ለማስቀርቀር ብሎም ዝም ለማሰኘት ይቻላል በሚል እርምጃ መውሰድ ጀመሩ።ይህም የሕዝቡን ቁጣ እየቀሰቀሰው ይታያል። ረዳት ሳጅን ሽታዬ ወርቁም ታህሳስ 17/ 2005 ዓ.ም በገሳ ጨሬ ከተማ የተደረገው የመንግሥት ሠራተኞች ስብሰባ ላይ አካሄዱን ያወገዘው። ሕዝቡን ማፈን ተገቢ አይደለም ያለው።
የረዳት ሳጅን ሽታዬ ወርቁ ጥያቄና ላቀረበው ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽም የዚሁ ውሳኔ አካል ነው። በደረሰበት ጫናና እስራት የተነሳ ነው ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ለመኖር መቸገሩን ያስታወቀው። ይህንን የሚያደርጉ ካድሬዎች ነገ ከሕዝቡ ጋር የሚኖሩ ናቸው ወይስ አይደሉም? እያልኩ ራሴን ስጠይቅ ምላሽ አጣለሁ። መንግሥትም የዳውሮ ሕዝብ ችግርን በመናቅ ጉዳዩ ለስልጣኑ ምንም የሚያሰጋው ስላልሆነ ይመስላል እስከዛሬ እያስለቀሰው ይገኛል።
ይህንን የዳውሮን ሕዝብ በደል ለማስቆም ትልቁ ጉልበት ያለው በመንግሥት እጅ መሆኑ ግልጽ ነው። መንግሥት ግን ስለ ሕዝቡ መበደል አልተገነዘበም ወይም ንቆታል አሊያም ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ዳውሮ ውስጥ ከፈጠራቸው አሽከሮቹ የሚቀርበውን የሐሰት መረጃ በመቀበል ሕዝቡን እንደጠላቱ ፈርጆታል ብዬ እገምታለሁ። በመሆኑም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚመለከታችሁ የሕብረተሰቡ አካላት የየድርሻቸውን መወጣት እንደ አለባቸው በማመን መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
መልዕክት ለሕወሀት አመራሮች
የዳውሮ ሕዝብ በደል እጅግ ተባብሷል። ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ያገኛል ብሎ ተስፋ ያደርግ ነበር። የሕዝቡ ጥያቄ በአጭሩ፤ የወረዳ ማዕከል ቦታ እንዲሆን የተመረጠው ሥፍራ የወረዳውን ሕዝብ አያማክልም፤ የወረዳ ዋና ከተማ ዝውውር የተወሰነውና የተከናወነው በአንድና ሁለት ካድሬዎች የግል ፍላጎትና መነሻነት ነው፤ ስለዚህ በሕዝቡ ፍላጎትና ሕዝቡን በሚያማክል ሥፍራ ይደረግልኝ ነው። ቅን መሪ ቢኖርና የመወሰን ኃላፊነት ከተመጣጣኝ ሥልጣን ጋር የተሰጠው ዜጋ ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንደማይቸገር ግልጽ ነው። ይህ ባለመሆኑ ሕዝቡ ተበደለ።