January 18, 2014
(ግንቦት 7) ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባችን ስለራሱና ሰለአገሩ ምንም አይነት መረጃ ከአማራጭ የመገናኛ ብዙሃን ምንጮች እንዳያገኝ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ድርግም አድርጎ ዘግቶ ኖሮአል።
የወያኔ መሪዎችና ተሿሚዎች በየግላቸው ምንም ቁብ በማይሰጡትና ተቃዋሚዎች እንዲያከብሩት ነጋ ጠባ በሚወተውቱት የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀጽ 29 ዕውቅና ካገኙ የዜግች መብቶች አንዱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ ሳለ እየተካሄደ ያለውን የሥልጣን ብልግናና አገሪቱን እያራቆተ ያለውን ዘረፋ በመተቸታቸው ብቻ በአንድ ወቅት እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የነጻ ጋዜጣ አዘጋጆችና አሳታሚዎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ከፊሉ ከአገር እንዲሸሽ ሌላው አፉን ዘግቶ እንዲቀመጥ አለያም የፈጠራ ክስ እየተመሰረተባቸው እስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል። አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው። በወያኔ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አፈና የአሜሪካና የጀርመን መንግሥታት በየግላቸው የሚያስተዳድሩዋቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮኖች እንኳ ከጥቃቱ ማምለጥ ስላልቻሉ እነሆ እስከዛሬ ያልተቋረጠ የማጥላላት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል።
ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ከቻሉና ከየትኛውም መዲያ መረጃ የማግኘት መብታቸው ከተረጋገጠ ሥልጣን ላይ ውሎ እንደማያድር ጠንቅቆ የተረዳው የወያኔ አገዛዝ በዚህ የሚዲያ አፈና ተግባሩ በመቀጠል ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮን እንዲሁም ህዝብ አልፎ አልፎ ሃሳቡን ለመግለጽ በሚገለገልባቸው ጥቂት የአገር ውስጥ ህትመቶች ላይ የተለመደውን የጥቃት ጅራፉን ለማሳረፍ ታጥቆ ተነስቶአል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በመረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ የህወሃት ቀድሞ ታጋዳላዮች በሚቆጣጠሩትና እንደግል ንብረታቸው በሚፈነጩባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከአሁን ቦኋላ ማንኛዉም የመንግስት ባለስልጣን፤ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ምንም አይነት ቃለመጠይቅ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ እንዳይሰጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል። ማስጠንቀቂያውን ተላልፎ በተገኘ ማንም ሰው ወይም ድርጅት ላይ የአሸባሪነት ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትበትም ዛቻና ማስፈራሪያ በተለመደው የቃላት ጋጋታ ተገልጾአል።
ይህ ከሰሞኑ የወያኔ ብሄራዊ መረጃ ደህንነትና ኮሚኒኬሽን መስሪያቤት ያወጣዉ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዜጎች የሚናገሩትን ፤ የሚጽፉትን፤ የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ብቻ ሳይሆን የሚያስቡትንና ሊደግፉት ወይም ሊቃወሙት ይችላል ተብሎ የሚጠረጠረውን ሁሉ አስቀድሞ ለመቆጣጠር ፍላጎቱ ያለው መሆኑን ነው።
ከሰሞኑ መግለጫ የተለየ ነገር ቢኖር ህዝባችንን በፍርሃት አንገት ለማስደፋት ሲባል የወያኔ ፓርላማ በሽብርተኝነት የፈረጀውን ንቅናቄያችንን ግንቦት 7ንና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንን በአንድነት የመፈረጅ ስልት ይፋ መደረግ መቻሉ ብቻ ነው።
የወያኔን ቁንጮዎች ጨምሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይገነዘበዋል ብለን እንደምናምነው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን ኢሳት የተቋቋመው የአገራቸው ጉዳይ የሚያንገበግባቸው ቅን ዜጎች ባዋጡት የገንዘብ መዋጮና በሚሰጡት ያልተቋረጠ የእውቀትና የፋይናንስ ድጋፍ ነው። ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 22 አመታት በወያኔ የሚዲያ ሞኖፖሊ ተይዞ የኖረውን የአገራችንን አየር ክልል ሰንጥቆ በመግባት ህዝባችን ስለ አገሩና ስለራሱ ጉዳይ በቂ መረጃ እንዲያገኝ በመጣር ላይ ያለ ብቸኛ መገናኛ ብዙሃን ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ ነው።
ሃቁ ይሄ ሆኖ ሳለ ለምንድነዉ ታዲያ ላለፉት ሁለት አመታት ስብሀት ነጋን ጨምሮ የተለያዩ የገዢዉ ፓርቲ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በተደጋጋሚ ቀርበዉ በስነ ስርኣት የተስተናገዱበትን ይህንን ሚዲያ የወያኔ ፓርላማ ቀደም ሲል በአሸባሪነት ከፈረጀው ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ጋር መወንጀሉ ለምን ይሆን ? መልሱ ቀላል ነው። ከአገዛዙ ያልወገኑ ማናቸውም ሚዲያዎች እንደሚያደርጉት ኢሳት ስርጭቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነጋ ጠባ በኢትዮጵያ ቴለቪዥንና ሬዲዮ የሚደሰኮረው ልማትና ዕድገት ተጠቃሚው ሥልጣንን የሙጥኝ ያሉ የቀድሞ ታጋዳላዮችና የቅርብ ዘመዶቻቸው እንጂ ህብረተሰቡ አለመሆኑን በግልጽ ከማጋለጥ ባለመቆጠቡ ጥርስ ውስጥ ገብቶአል። ከዚህም በተጨማር ለምዕራባዊያን ፍጆታና ድጋፍ ማግኛ በየአምስት አመቱ የሚደረገው የምርጫ ተውኔት ወቅት ስለተቃረበ ተቃዋሚዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው በዚህ ሚዲያ ያብጠለጥሉኛል፤ የስልጣን ብልግናውንና የሙስናውን ጉዳይ ይዘከዝኩታል የሚል ፍርሃትና ስጋትም አለው። በእርግጥ ዝክዘካው በይስሙላ ምርጫው ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ እኛ የጉዳዩ ባለቤቶች ቀርተን ምዕራባዊያን ለጋሾችም አያጡትም። ሆኖም ግን ወያኔ ፈርቶአል ተረብሾአል። ስለዚህም ኢሳትና አሁን በአክራሪ ድርጅቶች ልሳንነት የተፈረጁት የአገር ውስጥ ህትመቶች ከምርጫው በፊት መጥፋት ይኖርባቸዋል። ያ ካልሆነ በመላው አገሪቱ የሰፈነው የሥልጣን ብልግናና የሃብት ዘረፋ የፈጠረው የኑሮ ውድነት ያስመረራቸው ሚሊዮኖች የመጪውን ምርጫ ውጤት አስታከው ሆ ብለው አደባባይ ሊወጡና የአገዛዙን የሥልጣን እድሜ ለማሳጠር ተቃዋሚዎች ለሚያካሄዱት ትግል መሳሪያ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተፈርቶአል። ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከብዙ የወያኔ ጥቃትና አፈና ተርፈው አገር ውስጥ በመታተም ላይ በሚገኙ 8 መጽሄቶች እና ለኢትዮጵያዊያን ብቸኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ ላይ የተጀመረውን አዲሱን ዘመቻ በቸልታ አይመለከተውም።
መረጃ ሃይል ነውና አገራችን ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን፡ በመልካም አስተዳደር እጦት ሥር እየሰደደ የመጣው ድህነት እንዲቀረፍና ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚሻ ዜጋ ሁሉ ወያኔ በሚዲያ ላይ የጀመረውን ጥቃት ለማስቆም ከጎናችን እንዲሰለፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል።
ወያኔ በመረጃና ደህንነት መሥሪያቤቱ አማካይነት ያስተላለፈው የሰሞኑ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ በተለይም በሰላማዊና ህጋዊ ትግል ወያኔን መቀየር ይቻላል በማለት አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካና የስቪክ ድርጅቶች መተንፈሻ ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን ህዝባችን እንዲረዳና በህዝባዊ እምቢተኝነት ሴራውን ለማክሸፍ መነሳት ጊዜው ግድ የሚል የወቅቱ አንገብጋቢ የትግል ጥሪ መሆኑን ግንቦት 7 የፍትህና የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያስገነዝባል።
No comments:
Post a Comment