Monday, February 25, 2013

በኒውዮርክና በአካባቢው ከምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የተሰጠ መግለጫ


እኛ በኒውዮርክና በአካባቢው የምንገኝ ምዕመናን በቅርቡ ከህጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወቅታዊውን የቤተክርስቲያናችንን ሁኔታ በሚመለከት የተሰጠውን መግለጫ ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ መሆናችንን ለሚመለከተው ሁሉ ለመግለጽ እንወዳለን።

እንደሚታወቀው ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው በደል ያስከተለው ሀዘንና ጉዳት በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፣ በመሆኑም የቤተ
Ethiopian-Orthodox-Church-Holy-Synod

ክርስቲያኑ ካህናትና ምዕመናን ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ዕርቀ ሰላም እንዲወርድና ሕገ ቤተክርስቲያን እንዲከበር ሲመኙና ሲጸልዩ ኖረዋል። ከዚህም ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው እንዲል የሰላምና የአንድነት ጉባኤ በማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ባሉት አባቶች መካከል ዕርቅ እንዲፈጠርና ቀኖና ቤተክርስቲያንም እንዲከበር ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው ሲያስመሰግናቸው ይኖራል። ሆኖም ግን የመጨረሻው ድርድር ፍፃሜ ሳያገኝ ከአዲስ አበባው ሲኖዶስ የተሰማው ድምፅ ካህናቱንና ምዕመናኑን ከበፊቱ ለከፋ ሀዘን ዳርጎታል። በዚህም የተነሳ “ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለጋኔን” በሚል ርዕስ ከህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሰፊ መግለጫ ተሰጥቷል። እኛም በኒውዮርክና በአካባቢው የምንገኝ ምዕመናን ከሁለቱም ወገን የተሰጡትን መግለጫዎች በጥልቅ በመመርመር እውነትን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው ተብሎ እንደተጻፈ በውጭ ሀገር በሚገኘው ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠውን መግለጫ ሙሉ በሙሉ በመደገፍና በውስጡም የተሰጡትን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል ቆርጠን ተነሥተናል።

በመግለጫው ገጽ 6 ቁጥር 3 ላይ የተገለጸውን መመሪያ መሠረት በማድረግ እኛ በኒውዮርክና በአካባቢው የምንገኝ ምዕመናን የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፈናል፡፤
1ኛ/ ባለፉት 21 ዓመታት ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾሙ ያስከተለውን ጥፋት ለማረምና ለማስተካከል የተፈጠረውን ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅሞ ህጋዊውን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስን ከነሙሉ ክብራቸው ወደ መንበራቸው በመመለስ ፋንታ በጥፋት ላይ ጥፋት ሌላ ስድስተኛ ፓትርያርክ ለመሰየም የሚደረገውን ጥድፊያ እንቃወማለን፣ ተመራጩንም አንቀበልም።
2ኛ/ የተለያዩ መንፈሳዊ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት፣ ማኅበረ ምዕመናኑ ስለቅዱስ ሲኖዶስ አመሠራረትና ስለ ቀኖና ቤተክርስቲያን መከበር አሰፈላጊነት፣ ጥርት ባለ መንገድ እንዲገነዘብ
በማድረግ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላም ለቤተክርስቲያናችን ፍቅርና አንድነት በሙሉ ልብና በሙሉ ኃይል እንዲነሳ ያለሰለሰ ጥረት እናደርጋለን።

3ኛ/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው የመከፋፈል አደጋ የኢትዮጵያና የውጪ በሚል ብቻ አላበቃም። ከሁለቱም ያልወገነ ገለልተኛ በሚል ስም የሚጠራ ሦስተኛ አካል እንዳለ ይታወቃል። ቅድስት ቤተክርስቲያናችን አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት በአሁኑ ወቅት ሰላምና አንድነት ዕውን ለማድረግ እርምጃ መውሰድ የግድ ይላል። ስለዚህ፣ በሰላምና አንድነት ኮሚቴ አማካይናት በህጋዊው ሲኖዶስና በገለልተኛው ወገን መሀከል አንድነት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ የዕርቅ ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀምር በትህትና እንጠይቃለን።
4ኛ/ በህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከምን ጊዜውም በበለጠ የቅዱስ ሲኖዶሱን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል የሚፋጠን ልዩ ኮሚቴ እንዲቋቋም መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን፣ በዚሁም መሠረት በኒውዮርክና በአካባቢው ቤተክርስቲያናት ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን መጀመሩን በትህትና እንገልጻለን።
ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም፣ ስለቅድስት ቤተክርስቲያናችን ፍቅር አንድነት እንማለዳለን

No comments:

Post a Comment