Thursday, February 14, 2013

በስዊድን 136 000 ክሮነር ለኢሳት ተሰበሰበ


*የገንዘቡ መጠን በስዊድን ከክብረወሰን ተመዝግቧል

*ሙስሊሙና ክርስቲያኑ አንድነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳይቷል

Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. February 11, 2013)፦ ቅዳሜ የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም በተካሄደው
Artist and activist Tamagne Beyene in Sweden
 የኢሳት (የኢትዮጵያ ሳተላይ ቴሌቭዥን) የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 136 ሺህ የስዊድን ክሮነር የተሰበሰበ ሲሆን፤ በዚህ ዝግጅት ላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተሳትፎ ያደረጉበት መሆኑ ታውቋል።

አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በተገኘበት በዚሁ ዝግጅት ላይ ወደ ሦስት መቶ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን፣ ወጣት ኤርትራውያን እንዲሁም ስዊድናውያን ተገኝተዋል። ዝግጅቱ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ይጀምራ የተባለ ቢሆንም፤ ከሁለት ሰዓት በላይ አርፍዶ ተጀምሮ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ተጠናቅቋል። በስዊድን ከተደረጉ ዝግጅቶች ውስጥ ይኸኛው ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ አንድነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያሳየበት መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለመረዳት ችሏል።
በዝግጅቱ ላይ የስዊድን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርላማ አባልና የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ተወካይ የሆኑት ክብርት ካሪና ሄግ እንዲሁም በኢትዮጵያ ታስረው ከነበሩት የስዊድን ጋዜጠኞች አንዱ ማርቲን ሺቤ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
Ethiopian Muslims and Christians in Sweden
ዝግጅቱን በንግግር እንዲከፍቱ የተጋበዙት የክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖት አባቶች ነበሩ። እነርሱም ቀሲስ ፍሰኀ ከክርስትናው እና አቶ ሶፊያን ከእስልምና ኃይማኖት ሲሆኑ፣ ሁለቱም አባቶች ጎን ለጎን በመቆም ባደረጉት ንግግር የታዳሚዎችን ቀልብ የሳበ ንግግር አድርገዋል። የኃይማኖት አባቶቹ የኢትዮጵያን ታሪክ ከኃይማኖቶቻቸውን ጋር በማገናኘት በኢትዮጵያ ውስጥ የሁለቱ ኃይማኖቶች ምዕመናን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 1434 ዓመታት ተከባብረው በሠላምና በፍቅር መኖራቸውን ገልጸዋል። አክለውም ኢሳትን በሁሉም አቅጣጫ በሞራል፣ በማቴሪያል፣ በገንዘብ፣ በሙያ፣ … የመደገፍ የሁላችንም የሕሊና ግዴታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ካሪና ሲሆኑ፣ እንዲህ ኢትዮጵያውያን በጋራና በሕብረት የተሰበሰቡበት ዝግጅት ላይ ተገኝተው አብረዋቸው ዕለቱን በማሳለፋቸው የተሰማቸውን
Ethiopians in Sweden, ESAT fundrise
 ደስታ ገልጸዋል። ከተለያዩ የኢትዮጵያና የስዊድን አካባቢዎች የመጡትና እንዲህ በጋራ ተሰብስበው ሕብረትና ጥንካሬ ያላቸውን ኢትዮጵያውያኖችን ማየታቸው እንዳስደሰታቸውና ለኢትዮጵያም ቢሆን የሚያስፈልጋት ይኼው ሕብረትና አንድነት እንደሆነ ገልጸዋል። የተሰነጠቀ ዲያስፖራ መኖር እንዳይኖር አሳስበዋል።

የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር እና የአሁኑ የአዲስ ነገር ኦንላይን ድረ ገጽ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ እና በስቶክሆልም የኢትዮጵያ ራዲዮ ኃላፊ አቶ አህመድ ዓሊ የነፃ ሚዲያን ምንነትና አስፈላጊነት በማስመልከት ያዘጋጁትን ጽሑፎች አቅርበዋል።
Tamagne in Sweden for ESAT
ገጣሚ ማትያስ ከተማ (ወለላዬ) ”ዳግም በድል አብራ!” በሚል ርዕስ ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ያዘጋጀውን መወድስ አስደምጧል። ይህ መወድስ ሲነበብ ታዳሚው በሙሉ ከመቀመጫው ተነስቶ ለታማኝ ያለውን አክብሮት በጭብጨባ ገልጿል።
በመቀጠልም አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚዲያን አስፈላጊነትና የኢሳትን ሥራ ለታዳሚው እያዝናና አስተምሯል። በኢትዮጵያ የነበሩትና
Ethiopian artist Tamagne Beyene in Sweden
 አሁን ያለውን ሥርዓት ምን ይመስሉ እንደነበርና እንደሚመስሉ በቪዲዮ፣ በድምጽና በምስል እና በንግግር በሰፊው ተንትኗል። ይህ የታማኝ ዝግጅት ብዙዎችን ያስደሰተና ያረካ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ አዘጋጅ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

ከፍተኛውን የገቢ ማሰባሰቢያ ገንዘብ ያስገኘው ለጨረታ የቀረበው የሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ምስል ሲሆን፤ ጨረታው ከ500 ክሮነር ተነስቶ በ136 ሺህ የስዊድን ከሮነሩን ተጠናቅቋል። ከዚህ ሌላ በመግቢያ ትኬት፣ በምግብ እና በመጠጥ የተገኘ ገቢ ሲኖር፤ ለጊዜው መጠኑ አልታወቀም። በዕለቱ ምንዛሪ 136 ሺው ክሮነር ከሃያ ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሆነ ታውቋል። በስዊድን የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ እስከዛሬ በአንድ ቀን ካሰባሰቡት የገንዘብ መጠን ውስጥ ይህ የቅዳሜው ዝግጅት ላይ የተሰበሰበው 136 ሺህ ክሮነር ክብረወሰኑን (ሪከርዱን) መያዙን ለመረዳት ችለናል።

በጨረታው ወቅት ብዙዎች በታሰሩት ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ሙስሊሞች ስም ጨረታውን ሲጫረቱ ነበር። ከዚህም ሌላ በታሰሩት ጋዜጠኞች ልጆች፣ በዕለቱ ልደቷን በእስር ሆና በምታከብረው በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ በታማኝ በየነ፣ በጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች ስም ታዳሚዎች በጨረታው ተሳትፈዋል።
ጨረታው ከመጀመሩ በፊት ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ ስለአቡነ ጴጥሮስ ታሪክ ያዘጋጁትን ጽሑፍ በንባብ አሰምተዋል።
ጨረታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የስዊድን የኢሳት ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ያላቸውን ሽልማትና ስጦታ አበርክተውለታል። በመቀጠልም አክቲቪስት ታማኝ ዝግጅቱን ላዘጋጁት ወገኖች የሜዳሊያ ሽልማት ሰጥቷል።
ዝግጅቱን በየመሃሉ የተለያዩ አርቲስቶች በባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ ድምቀት ሲሰጡት አምሽተዋል። በመጨረሻም ከአክቲቪስት ታማኝ ጋር ታዳሚዎች የፎቶ ሥነሥርዓት አካሂደው ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ዝግጅቱ ተፈጽሟል። (ይህንን ዝግጅት አስመልክቶ ጠለቅ ያለ ሪፖርት ለማቅረብ እንሞክራለን።)
አክቲቪስት ታማኝ በየነ በአውሮፓ ሰባት ሀገራት ለኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከስዊድን ቀደም ብሎ በስዊዘርላንድ ተገኝቷል። ከስዊድኑ ዝግጅት በመቀጠል በማግስቱ እሁድ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በኖርዌይ ዋና ከተማ በኦስሎ ወደተካሄደው ዝግጅት አቅንቷል። ከነዚህ ሦስት ሀገራት በተጨማሪ በጀርመን ሙኒክ (ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 16)፣ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም (እሁድ ፌብሩዋሪ 17)፣ በእንግሊዝ ሎንዶን (ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 23) እና በቤልጅየም ብራስልስ (እሁድ ፌብሩዋሪ 24) ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ታውቋል።

No comments:

Post a Comment