Saturday, January 12, 2013

በ አዲስ አበባ የወላይታ ተወላጆች እየታፈሱ ነው


በተለያዩ ጥቃቅን የንግድ ሥራዎች ተሰማርተው የሚገኙ የወላይታ ተወላጆች”ወደ አካባቢያችሁ ትመለሳላችሁ”ተብለው ታፍሰው መታሰራቸውን ፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሊስትሮነትና በሌሎች ጥቃቅን ንግዶች ተሰማርተው የነበሩ በርካታ የወላይታ ተወላጆች “የጸጥታ ስጋት ናቸው”ተብለው  በፌዴራል ፖሊስ ታፍሰው ታስረዋል።
እንደ ወኪላችን መረጃ በትናንትናው ዕለት ብቻ 130 የወላይታ ተወላጆች አራት ኪሎ አካባቢ በፖሊስ ታፍሰው ሜክሲኮ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ  ታስረዋል።
መጀመሪያ በተደረገው አፈሳ እጅግ በርካታ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ዜጎች  በጅምላ መታፈሳቸውን የገለጹት የፖሊስ ምንጮች፤ ሁሉም ከታሰሩ በሁዋላ መታወቂያቸውን እንዲያሳዩ እየተደረገ የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች ሲለቀቁ የወላይታ ተወላጆች ብቻ  እየተመረጡ ታስረው እንዲቆዩ  ተደርጓል።
የወላይታ ተወላጆች በአካባቢያቸው ባለው አስከፊ ኑሮ የተነሳ በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንደሚሰደዱ ይታወቃል።
ተወላጆቹ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የጸጥታ ስጋት ደቅነዋል በሚል ሰበብ ታፍሰው ወደ መጡበት እንደሚለሱ ለማድረግ እንቅስቃሴ ቢጀመርም ዋነው ምክንያት ግን ለከተማዋ ገጽታ መበላሸት አስተዋጽኦ አድርገዋል በሚል ነው። አንዳንዶቹ  በድህነት ምክንያት  በቤተክርስቲአኖችና በጎዳናዎች ላይ እንደሚያድሩ ይታወቃል።
ኢህአዴግ የሚከተለው ዘርና ቋንቋን ማዕከል ያደረገ ፌዴራሊዝም፤ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በአገራቸው በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ እንቅፋት መፍጠሩን፤ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ አብነቶችን በማሳየት ሲተቹ ይደመጣሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር  ሀይለማርያም ደሳለኝ የወላይታ ተወላጅ መሆናቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment