Sunday, October 28, 2012

አስደሳቹ የብሔራዊ ቡድን ውጤትና ቅሌት


ባሳለፍናቸው ሳምንታት  እሁድ ዕለት አንበሳው የብሔራዊ ቡድናችን ያደረገው ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ትንቅንቅ በጣም አጓጊና አስደሳች እንደነበር አይተነዋል።  ጀግናው ብሔራዊ ቡድናችን የሱዳን አቻውን  ሁለት- ለዐልቦ  በሆነ ውጤት በዝረራ አሸንፎ እነሆ ከሰላሳ አንድ አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድናልፍና  ልክ  አረንጓዴ ጎርፍ ተብለው የሚጠሩት አትሌቶቻችን ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርገን እንድናውለበልብ እንዳደረጉን ሁሉ ዛሬም ብሔራዊ ቡድናችን አፍሪካ ላይ ለጊዜውም ቢሆን መሀሉ ላይ የሰይጣን አምልኮት ምልክት ያለበትን ባለኮከቡን  አረንጓዴ ፥ ቢጫና ፥ ቀዩን ሠንደቅ ዓላማችንን እንድናውለበልብ አድርገውልናል ፡፡ ምስጋና ይግባቸው ለዋልያዎቹ ።
ይህን ድል አቶ መለስ በህይወት ኖረው ቢያዩት ደስ ይለኝ ነበር። የሚሉትን ለመስማት ፡፡ ግን አፈር ይክበዳቸውና የሉም። ሀገራችን ኢትዮጵያን እግዚአብሔር አምላክ በቸርነቱ እንደሚጠብቃት ብዙ ምልክቶችን አሳይቶናል። ለዚህም ለአብነት ያህል፦ አዲስ አመት መግቢያ ግድም ዘረኛውንና አምባ ገነኑን፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይነት ደንታ የሌለውን፥ ህዝቡን በዘር የከፋፈለውን ፥ አረመኔ መሪ መለስ ዜናዊንና ቋሚ የሲኖዶስን ህግ ጥሶ በአጉራዘለልነት  በራሱ ፈቃድ የሾማቸውን ጭፍራውን አባ ጳውሎስን ጨምሮ ከምድረ ገዕ እንዲጠፉ አድርጓቸዋል። ሎሚ ተራ ፥ ተራ ነውና ሌሎቹንም ተራ በተራ  እንደሚጠርጋቸው አልጠራጠርም ፡፡ በቅርብ የምናየው ይሆናል ።
ለሃያ አንድ ዓመታት ግራ – ሸቅብ ብለው በሃገሪቷ ላይ የጨበጠትን መዳፋቸውን አዲሱ አመት አስፈልቅቆ ጠላቶቿን ስለቀነሰላት  አዚማቸው ከሽፎ ፣ ብሄራዊ ቡድናችን ብቻ ሳይሆን ፥ የወጣት ቡድኑም ሆነ ፥ የሴቶቹ ሉሲ የእግር ኳስ ቡድን ጭምር ኢትዮጵያን ወክለው በአፍሪቃ ውድድሮች ውስጥ ዘንድሮ እንዲካተቱ አምላክ ፈቅዷል ፡፡
በቅድሚያ ግን ለስፖርት ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ስፖርት አፍቃሪ ህዝብ  በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ ። መጨረሻውንም እንዲያሳምርልን እየተመኘሁ ፣ አንድ ቅር ወደተሰኘሁበት ጉዳይ ላይ ግን በቀጥታ ላምራ ፡፡ ድሉን ያስጨበጡን ዋልያዎቻችንና  የወቅቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝን ጨምሮ፣  ለጋዜጠኞች የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግን እጅግ አስተዛዛቢ ነበር ፡፡ እማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ ሆኖባቸው እንደሆነም ልቦናዬ ጠንቅቆ ያውቃል ፡፡  ልማታዊ እስፖርተኝነትና የካድሬ ሥራ ሆኖባቸው ተጫዋቾቻን ፣ አቶ መለስ በህይወት ዘመናቸው የኢትዮጵያ የግር ኳስ ቡድን ላይ የተዛበቱትን በመርሳት መታሰቢያነቱ ለአቶ መለስ ይሁንልን ማለታቸው ግን አንጀቴን  ነው ያቃጠለው ።
መሬት ይቅለላቸውና ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እንኳንም በዚህ ዘመን  ያልኖሩ ፡፡ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ኳስ ተጨዋች አይብቀልብሽ ብለው አገሪቷን ይረግሟት ነበር ፡፡  አቶ መለስ በአንድ ወቅት ስለ ብሔራዊ ቡድናችን ተጠይቀው የመለሱትን መልስ ላስታውሳችሁ ፡፡ በዚያን ወቅት  አቶ መለስ የጦር ኃይላችንን ወደ ሶማሌ ለማዝመት ደፋ ቀና የሚሉበት ወቅት ነበር ፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ፦ ወደ ሶማሌ ተልኮ የሄደውን የኢትዮጵያ ወታደር እንደከዚህ በፊቱ አሜሪካዊ ወታደር  ሬሳውን በመኪና ሲጎትቱት  የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያይ ምን የሚልዎት ይመስሎታል ? ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ  የመለሱት መልስ ፦ ለጦርነት የሚሄደው እኮ ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት እንጂ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን አይደለም በማለት አሳዝነውናል።
በሌላ ወቅት ደግሞ ብሔራዊ ቡድናችን ከሀገር ውጪ ሊጫወት ሄዶ በሙሉ ተጫዋቾቹ ሳይመለሱ ቀሩ ተብለው ሲጠየቁ ፦ መንገዱን ጨርቅ ያርግላቸው ይህ እኔን አያሳስበኝም ፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ አንድ ገበሬ ቢጠፋ ነው ብለው መልሰዋል።  እንደውም ስታዲየሙን ቢለቁልን ማዳበሪያ ፋብሪካ እንከፍትበታለን በማለትም ጭምር በብሄራዊው ቡድን ላይ ተዛብተውበታል ፡፡  ታዲያ እንግዲህ ጎበዝ ለዚሁ በብሔራዊ ቡድናችን ላይ በሞራሉ የተረማመደበትንና በቡድኑ አናት ላይ ቀለበት መንገድ የሰራበትን መሪ ነው መታሰቢያነቱ ለሱ ይሁን ብለውአሰልጣኝና ተጨዋቾች ያስደመሙን ።
ማን ያውቃል ! ከእጅ አይሻል ዶማ እንዲሉ አቶ ሀይለማሪያምና ጭፍሮቻቸውም አስገድደዋቸው ይሆናል ስፖርተኞቻችን ልማታዊ ስፖርተኞች የሆኑብን ፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን መታሰቢያነቱ ለአቶ ይድነቃቸው ተሰማና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪ በሙሉ ቢሆን በጣም ደስ ይለኝ ነበር ግና አልሆነም ። እንግዲህ ገዢው የኢሕአዴግ ፓርቲ ሲገረሰስና ሙሉ ለሙሉ ከስልጣን ሲወገድ የብሔራዊ ቡድናችን ዝናና ክብረ ሞገስ ልክ እንደ ሶስተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ጀግንነታችን መመለሱ አይቀርም ፡፡ ጅምሩንም በዚህ አዲስ አመት አይተናልና ፡፡ ለአለም ዋንጫም አገራችን እንደምትደርስ አንጠራጠርም ፡፡  ያኔ ታዲያ ማስታወሻነቱ ለማን ይሆን ? ቸር እንሰንብት ።
ውድቀት ለወያኔና ጭፍሮቹ እግዚአብሔር ኢትዮጲያን ይባርክ !!

No comments:

Post a Comment