የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 32ኛ አመት ለማክበር አርብ ምሽት በጅዳና በአካባቢዋ በተዘጋጀ ዝግጅት ለመሳተፍ የሄዱ በርካታ ነዋሪዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውንና ስብሰባው በጊዜ መበተኑን ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ ከስፍራው ገልጿል።
ዛሬ በተጠራው የብአዴን ዝግጅት ላይ የተቃውሞ ድምጻችን እናሰማለን በሚል ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ወረቀት በህቡዕ የበተኑ ሲሆን፤ በስብሰባው ላይ ተቃውሞ እንዳያካሂዱ በሚል ፍራቻ ጥሪ የተደረገላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ከስብሰባው ውስጥ እየተጠሩ እንዲባረሩ መደረጉን ነዋሪዎች ለነቢዩ ሲራክ ገልጸውለታል።
ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ መታዎቂያ አሳዩ የሚል ምክንያት ለመስጠት የተሞከረ ቢሆንም፤ መታወቂያ ይዘው የተጠረጠሩና የተፈሩ አንዳንድ ነዋሪዎችም ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ እንደተደረጉ ታውቋል፡፡
የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ በባንዴራ አጅበው ከኮታቸው ላይ የለጠፉ የብአዴን አባላት ነዋሪዎችን በጥርጣሬ አንዳይገቡ ሲከለከሉና የፈለጓቸውን እየመረጡ ሲያስገቡ እንደታዘበ ነቢዩ ሲራክ ከስፍራው ዘግቧል።
ከመግቢያው በር ያሉትን የሳውዲ ልዩ ኮማንዶ ወታደሮችን ያናገረው ነቢዩ ሲራክ፤ ”የቆንስሉ ሃላፊዎች ማንም እንዳይገባ ከልክሉ ብለውናል” በማለት እንዳስረዱትና ነዋሪውን በማግባባት ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ሲማጸኑ እንደተመከተም ገልጿል።
የብአዴን አባላት እገዳው የተደረገው በጸጥታ ምክንያት እንደሆነና ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተጠረጠሩና የማይታወቁ ሰወች እንዳይገቡ እገዳ መጣሉን ገልጸዋል።
አንዳንድ የብአዴን አባላት በጥሪ የመጡትንም እያንጓጠጡ ያስወጧቸው ሲሆን፤ ስብሰባው ያለወትሮው በጊዜ ሲጠናቀቅ ከስብሰባው የወጡ አንዳንድ ሰዎች ሲገቡ ችግር እንደገጠማቸውና በስብሰባው ላይ ምንም አይነት ፎቶም ሆነ ቪዲዮ እንዳይነሳ ቁጥጥር መደረጉንና ስብሰባው በተቃውሞና ፍራቻ ሲናጥ ማምሸቱን እንደገለጹለት ነቢዩ ሲራክ ከጂዳ ገልጿል።
No comments:
Post a Comment