ጉጅሌዎቹ ኢትዮጵያን መግዛት ከጀመሩ ዘመን ጀምሮ በአገራችን የንፁህ ሰው ደም ሳይፈስ የዋለበት ቀን የለም። ኢትዮጵያችን በየቀኑ የንፁህ ሰው ደም የሚፈስባት አገር ሁናለች። ዜጎችም ይሄን የለመዱት ስለሆነ ሰው ሞተ ሲባል ብዙም አይደነቁም። ጉጅሌዎቹ ደግሞ አንድ ያለፈባት ብሂል አለቻቸው እንዲህ የምትል፤
ግደሉ ግደሉ ሰው መግደል ይበጃል፤
ሰው ያልገደለ ሰው ሲሄድ ያንጎላጃል።
ይህች የአንድን ማህበረሰብ የስነ ልቦና ቀውስ ደህና አድርጋ የምታሳይ ቅኔ የህወሃቶች ስንቅና ትጥቅ ነች። ይህችን ቅኔ ታጥቀው በየደረሱበት የንፁህ ደም ሲያፈሱ የሂሊና ወቀሳ የለባቸውም። እዚህም ይገድላሉ፤ እዚያም ይገድላሉ። ለህወሃቶች ሰው መግደል ክፉ ነገር አይደለም። ሰው መግደል ለስልጣን የሚያበቃ፤ ስልጣን ላይም እስከ ፍፃሜው የሚያቆይ የጎበዝ ምግባር ነው የሚል የማይናወፅ እምነት አላቸው። ይህን ዕምነታቸውንም የገለጡበትን መንገድ ትንሽ ወደ ኋላ ሂዶ በሃውዜን ህዝብ ላይ ያስፈፀሙትን ጭፍጨፋ ማስታወስ በቂያችን ይሆናል።
ጉጅሌዎቹ ጥልቅ በሆነ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ። ከግል ህይወታቸው ጀምሮ እስከ ጨበጡት የስልጣን እርከን ድረስ ንፅህና የጎደላቸው፤ በንፁሃን ደም እጃቸው የተጨማለቀ ነው። ይህ ነውራቸውም ሁሉንም እንዲፈሩ፤ በሁሉም እንዲደነግጡ አድርጓቸዋል።ከዚህ ፍርሃትና ድንጋጤም ለመላቀቅ የተዘፈቁበት የወንጀል መዓት የሚያስችላቸው አልሆነም። እነርሱም ከጥፋታቸው ተምረው እንደ ሰው ልጅ ለማሰብ ፍላጎቱ የላቸውም። የጉጅሌዎቹ የልብ ድንደና የመፅሃፍ ቅዱሱ የፈርዖንን ልብ ድንደና ይመስላል። የፈርዖንን የመጨረሻ ታሪክ ያየ ግን ልቡን ከማደንደን ይልቅ የህዝቡን ጩኽት መስማትን ይመርጥ ነበር። ይሄም ቢሆን ብልህነትን ይጠይቃል።አገራችን ከተደቀኑባት ብርቱ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኛው ጉጅሌዎቹ ብልህነት ያልፈጠረባቸው ሁሉንም በጠብ-መንጂያ እናሸንፈዋለን ብለው ከልባቸው ማመናቸው ነው። ይሄም እምነታቸው ነው በህግ ጥላ ሥር ያሉትን እንኳ ሳይቀር ቀጥቅጠው እንዲገድሉ የሚያደርጋቸው።
በዓለማያ ዩንቨርስቲ ውስጥ ወለጋ ክለብ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ ቦንብ ፈንድቶ ተማሪዎች መጎዳታቸውን የነገረን ህወሃት ነው። ጉጅሌዎቹ እኛ ከመጣን በኋላ ሠላም ሆነ እያሉ በሚያላዝኑበት አገር ውስጥ ይህን መሰሉ እኩይ ተግባር እንደምን ሁኖ ሊፈፀም እንደቻለ በቂ ማብራሪያ የላቸውም። ብዙ ተማሪዎች ከተጎዱ እና ህይወትም ከጠፋ በኋላ ጥፋተኞቹን ያዝኩ ሲልም ያወጀው አሁንም ጉጅሌው ነው። ከተያዙት መካከልም አንዱ ኑረዲን ሃሰን በእስር ቤት እንዳለ ህይወቱን አጠፋ መባሉንም የሰማነው ከጉጅሌዎቹ ነው። በህግ ጥላ ሥር የሚገኝ አንድ ሰው ፍትህ እሰከሚያገኝ ድረስ በህይወት እንዲቆይ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ የመንግስቱ ኃላፊነት ነው። ለዚህም ሲባል ቀበቶው ተፈቶ፤ ሌሎች በራስ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮች ሁሉ ተፈትሸው በዕስር ቤቱ ኃላፊዎች እጅ እንዲቆዩ ይደረጋል። ራሱን ገደለ የተባለው ኑረዲን ሃሰንም ቢሆን በማረሚያ ቤቱ ህግ መሠረት ተገቢውን ፈፅሟል።
ታዲያ እንደምን ሁኖ ኑረዲን ሃሰን ራሱን ሊያጠፋ ቻለ ለሚለው ጥያቄ የጉጅሌው ቡድን የሠራውን ያውቃልና የሆነውን አይናገርም።ወጣቱ ራሱን አላጠፋም። ኑረዲን ሃሰን ብርቱ የሆነ የመኖር ምኞት እና የራሱ ራዕይ የነበረው ወጣት ነበር። ይህን ወጣት ቀጥቅጠው ገድለው ተስፋውን ያጨለሙት የጉጅሌዎቹ ጀሌዎች መሆናቸውን ደርሰንበታል። የኑረዲን ሃሰንን ህይወት የቀጠፈው ግለሰብም ሆነ ቡድን ህወሃት በስልጣን እስካለ ድረስ ለፍርድ እንደማይቀርብ የታወቀ ነው። እንዲያውም በህወሃት ባህል መሠረት ተመስግኖ ይሾማል ይሸለማል እንጂ ሌላ የሚሆን ነገር አይኖርም። እንግዲህ ህወሃቶች ከሚገለጡበት ነውር ተግባራት መካከል አንዱ የንፁህ ደም ያፈሰሰን ነፈሰ ገዳይ ለሹመት ማብቃታቸው ነው።
እነዚህ ቡድኖች እግራቸው በረገጠበት መንደር ሁሉ የንፁሃንን ደም በከንቱ ያፈሳሉ። ይሄ የታወቀው ልማዳቸው ነው። የንፁህ ሰው ደም አፍስሰው ሲያበቁም ከበሯቸውን እየደለቁ እና ምድሪቷን እያስጨነቁ ማን ይደፍረናል እያሉም ያጓራሉ።
ከዚያም ለሌላ ዙር ግዲያ ያበረታታቸው ዘንድ፡
ግደሉ ግደሉ ሰው መግደል ይበጃል፤
ሰው ያልገደለ ሰው ሲሄድ ያንጎላጃል።
እያሉ የሰው ደም መጠጣት ለለመደው አምላካቸው ቅኔ ይቀኙለታል።
እኛ ግን እንዲህ እንላለን ለሁሉም ግዜ አለው። የፍርድ ቀንም ሩቅ አይደለችም።እንደ ኑረዲን ሃሰን በየቦታው ተገድለው የተጣሉ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ናቸው። ብዙ ፍትህ ተነፍጓቸው በየሥፍራው እንባቸውን በመዳፋቸው የሚያፍሱ አሉ። ከነ ቤተሰቦቻቸው ሜዳ ላይ የተጣሉም አሉ። ብዙ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ በህወሃት የተፈፀሙ ሰቆቃዎች ሁሉ ተመዝግበው በጃችን አሉ። እነዚህ ሁሉ ቀናቸውን እየጠበቁ ነው። የእነ ኑረዲን ሃሰን፤ የእነ ህፃን ነብዩ፤ የእነ ወ/ሮ እቴነሽ ይማም፤ የእነ ሽብሬ ደሳለኝ፤ የእነ አቶ ደራራ ከፈኒ፤ የእነ አሰፋ ማሩ እና የሌሎች የብዙ ሺዎች ደም ከምድር ወደ ሰማይ እየጮኸ ነው። ይሄ ጩኸት መልስ የሚያገኝበት ቀን ፈጥኖ እንዲመጣ ትግሉ ተጧጥፎ በሁሉም መስክ መቀጠል ይኖርበታል። ሁል ግዜ እየገደልን እሰከ መጨረሻው እንዘልቃለን ማለት ቅዥት መሆኑንም ለጉጅሌዎቹ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
ጉጅሌዎቹ ብልህነት የሌላቸው ባይሆኑ ኑሮ የህዝብን ድምፅ ማድመጥ ይመርጡ ነበር። ከተዘፈቁበትም የቅዥት ዓለም ውስጥ ለመውጣት ምን እናድርግ ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። ግን ምን ያደርጋል ጉጅሌዎቹ ቅዥታቸውን እንደ ኃይማኖት አምነው ስለተቀበሉት ለሌላ እልቂትና ደም መፋሰስ ራሳችውን ያዘጋጃሉ እንጂ ከገቡበት ቅዥት ለመውጣት ምን እናድርግ ብለው አይጠይቁም።ይሄ ቅዥታቸው ነው እኛ ከሌለን አገሪቷ ትበተናለች፤ የጎሳ ግጭት ይነሳል፤ እልቂት ይሆናል እያሉ ያለምንም እፍረት ድምፃቸውም ከፍ አድርገው እንዲለፈልፉ የሚያደርጋቸው። እውነቱ ግን በአሁን ሠዓት ከማንም በላይ ለአገራችን ቀንደኛ ጠላት መሆንን የመረጡት ራሳቸው ህወሃቶች ናቸው። የአገሪቷና የህዝቧ ጠላት መሆንን በመምረጣቸውም ነው “እኛ ከሌለን አገሪቷ ትበተናለች” እያሉ የሚያቅራሩት። ይሄንን ግን ባዶ ማቅራራት አድርጎ መገመት ከስህተት ይጥላል።
ህወሃቶች ሆይ ስሙ! በህዝባችን መካከል ያለው ልዩነት እና የጭካኔያችሁ ልክ ማጣት እሰከ ዛሬ አቆይቷችኋል።ጭካኔንም ከጀግና ተግባር እየቀላቀላችሁ ተራራውን አንቀጠቀጥን እያላችሁ ያቅራራችሁትን ሁሉም ሰምቷችኋል። ህዝቡንም ድርና ማግ ሁነው በአንድነት ያቆዩትን ክሮች በጣጥሳችሁ ለመጨረስ ሌት ተቀን እንደምትባዝኑም የተሰወረ አይደለም።”እኛ ከሌለን አገሪቷ ትበተናለች” የሚባል ሟርትም ካልተገራው አንደበታችሁ መውጣቱንም በጥሞና አድምጠናል። ይሄ ቅዥታችሁ በቅዥት እንደሚቀር እኛ እንነግራችኋለን። እኛ ኢትዮጵያዊያን እያለን አገራችን አትበተንም። ምንም እንኳ የምትሰሩት ሁሉ የተራ ወንበዴ ተግባር ቢሆንም፤ ጭካኔያችሁ ወሰን ቢያጣ፤ ቅንጣት ታክል አገራዊ ኃላፊነት የማይሰማችሁ ብትሆኑም፤ በአገሪቷ ዜጎች መካከልም የጎሣ ግጭት ፈጥራችሁ በሚፈሰው ደም እጃችሁን ታጥባችሁ በኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ለመቀመጥ ብትመኙም አይሆንላችሁም።
የህወሃት ፖሊሲ የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው እያላችሁ እንደምታላዝኑም እናውቃለን።ይሄ የህዝብ ጠላት መሆንን መምረጣችሁን የሚያሳረዳ ሌላው ዓቢይ ነገር መሆኑን እንዳትረዱ ድንቁርናችሁና ትዕቢታችሁ ስለጋረዳችሁ አታስተውሉትም። የአገር እና የህዝብ ጠላት መሆን ማለት “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል” ብሎ ግትር ማለትን እንደሚጨምር ልናስታውሳችሁ እንወዳለን። ”እኛ ያልነው ብቻ” ስትሉ ለእውነትና ለህዝብ ፍላጎት ሳይሆን ለራሳችሁ የግል ጥቅም እንደምትሞቱ ያሳየናል። አገርና ህዝብ ደግሞ ከግለሰቦችና እናንተን ከመሰለ እኩይ ቡድን ፍላጎት በላይ ስለሆነ በያዛችሁት መንገድ ብዙ አትዘልቁም። ህዝብ የአገሩ ባለቤት ለመሆን በተገኘው አጋጣሚ እና ባለው አቅም ሁሉ ይታገላችኋል። አሁንም ትግሉ እየተፋፋመባችሁ ነው። ከውስጥና ከውጪ የሚደረገው ትግል ከመቸውም ግዜ በላይ ተደጋግፎ የማይናወፅ መሠረት ጥሏል። ”በመቃብራችን ላይ” ካለሆነ ብላችሁ ድርቅ ማለታችሁን የሰማ ሁሉ የአገሩ ባለቤት ለመሆን ጋሻና ጦሩን እያነሳ ነው። አሁንም ከግትርነታችሁ የማትመለሱ ከሆነ እድል ፈንታችሁ መሰበር ነው። እኛም ለዚያ እየተዘጋጀን ነው። ጀግና የሆነ በሊማሊሞ በኩል ይሞክረኝ ብሎ በገዛ ህዝቡ ላይ ጦርነት ያወጀው የጥፋት መሪያችሁ መለስ ዜናዊ በድንጋጤ ብቻ መሞቱን እናንተም እኛም ህያው ምስክሮች ነን። ከእናነት መንደር ፍርሃት እንጂ ጀግንነት የለም። ጀግና እኔ ብቻ ብሎ ድርቅ አይልም። ጀግና ከራሱ ጥቅምና ፍላጎት በላይ ለህዝብ የሞትለታል እንጂ ህዝብን አይገድልም። እናንተ እንደ ጀግና ለማሰብ የአስተሰሳብ ደረጃችሁ እጅግ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ጀግና እንደምን ያስባል ብትሉ ?
ጀግና እንዲህ ያስባል እንላችኋለን ”በሩቅም በቅርብም ያላችሁ ወዳጅና ጠላቶቻችን ሆይ ስሙ! እኛ ለኢትዮጵያዊያን ነፃነት፤ እኩልነት እና ፍትህ ስንል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል፤ የህዝባችንን በደል ልንሸከም፤ሁሉንም መከራ ልንቋቋም፤ ለህዝባችን ነፃነት፤ እኩነልት እና ፍትህ የሚታገሉትን ልንደግፉ፤ ነፃነትን የሚከለክሉትን፤ በዜጎች መካከል ቂምና በቀልን የሚተክሉትን፤ ፍትህን የሚያዋርዱትን ለመዋጋት ቆርጠን ተነስተናል”
የጀግና ሃሳብ እንዲህ ነው። እናንተ ግን እንዲህ ታስባላችሁ ብለን አንጠብቅም። ይሄ አስተሳሰብ ተፈጥሯችሁም ባህላችሁም አይደለም።ከግል ጥቅማችሁ ዘላችሁ ለእውነትና ለህዝብ ክብር የመቆም ባህል በእናንተ ውስጥ የለም። በእናንተ ውስጥ ያለው “ተኛ ሲባል የሚተኛ፤ ተነስ ሲባል የሚነሳ “ከንቱ ዜጋ የመፍጠር ምኞት ነው። ይሄን ምኞታችሁን የሚያመክን ወጣት እምቢ ብሎ ተነስቶ በግንቦት ሰባት ለፍትህ፤ ነፃነትና ለዴሞክራሲ በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተቀላቀለ ነው። እኛ እያለን አገራችን አትበተንም የሚሉ ተነስተዋል። ከእንግዲህም አታስቆሟቸውም። በመቃብራችን ላይ ብላችሁ እንደተመኛችሁት ሁሉ ምኞታችሁን ለማስፈፀም መሠረት የያዘ ትግል በሁሉም አቅጣጫ ተጧጥፎ ይቀጥላል።
በመጨረሻም ያፈሰሳችሁት ደም ከምድር ወደ ሰማይ እየጮኽ ነው። ብዙ ኢትዮጵያዊያንን እየገደላችሁ በጅምላ በየጉድባው እንደምትቀብሩም ታውቋል። ይሄን ሁሉ ግዲያ እንድትፈፅሙ የሚያደርጋችሁ የስልጣን ሥሥትና የንዋይ አፍቆሮታችሁ የሚርካ አልሆነም። እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያቂው የትግሬ ነፃ አውጪ ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራው ጎጠኛው ቡድን መሪዎች ናቸው። በዚያች አገር የሚፈሰው የኢትዮጵያዊ ደም ሁሉ ካለእነርሱ እውቅናና በጎ ፈቃደኝነት ውጪ አይደለም። ለእያንዳንዷ ላፈሰሳችሁት ደም ዋጋ የምትከፍሉበት ቀን እሩቅ አይደለም። በህይወት እያላችሁ ታያላችሁ ልጆቻችሁም ምስክሮች ይሆናሉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!