የአዉሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ሲቀራመቱ ባህር ተሻግረዉ በመጡ የነጭ ባዕዳን ኃይሎች መገዛትን መርጦ የአዉሮፓን ወራሪዎች በሰላም በሩን ከፍቶ ወደ አገሩ ያስገባ እንድም የአፍሪካ አገር አልነበረም፤ የኋላ ኋላ ተሸንፈዉ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ቢወድቁም ሁሉም የአፍሪካ አገሮች እንደ አቅማቸዉ ከወራሪ ኃይሎች ጋር ተፋልመዋል። በአንድ ወቅት የቅርብ ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች በወራሪ ኃይሎች ተሸንፈዉ የቅኝ ገዢዎች ቀንበር ጀርባቸዉ ላይ ሲጫን አገራችን ኢትዮጵያ ብቻዋን የአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆና የኖረችዉ ጣሊያኖች፤ እንንግሊዞችና ፈረንሳዮች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለይተዉ ስለወደዷት ወይም ስላከበሯት አይደለም። ይልቁንም ነፃነታችንና የግዛት አንድነታችን ተከብሮ የኖረዉ ኢትዮጵያ እናት አገሩ በጠላት ስትደፈር ከሚያይ ምትክ የሌላት ህይወቱ ብታልፍ ደስ የሚለዉ የኩሩና የጀግና ህዝብ አገር በመሆኗ ነዉ። የሚገርመዉ ይህ ኩሩና ጀግና ህዝብ ጣሊያንን የመሰለ በዘመናዊ መሳሪያ የታጀበ ኃይል ዉርደቱን ተከናንቦ ወደመጣበት እንዲመለስ ሲያስገድድ እንደ ዛሬዉ የተደራጀ ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት አልነበረዉም። ዛሬ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ላይ የተተከሉት ሁለቱ ታሪካዊ ሀዉልቶቻችን የሚነግሩንም ይሀንኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናዊ መልክ የተደራጀ ሠራዊት ሳይኖረዉ የጎበዝ አለቃ እየመረጠ በጣሊያን ፋሺስቶች ላይ የተጎናጸፈዉን አኩሪ ድል ነዉ።