Wednesday, December 5, 2012

ነጋዴዎች አዲስ ራእይ መጽሄትን እንዲገዙ እየተገደዱ ነው


ነጋዴዎቹ ለኢሳት እንደተናገሩት ፣ አንድ ነጋዴ በ100 ብር ቢያንስ ሁለት የአዲስ ራእይ መጽሄትን መግዛት ግድ ይለዋል። ይህን መጽሄት ለመግዛት ፈቃደኛ ካልሆ ጸረ ልማትና ጸረ ህገመንግስት ተደርጎ ይቆጠራል። መጽሀፉን የሚሸጡት የኢህአዴግ አባላት ሲሆኑ ፣ አንድ አባል በነፍስ ወከፍ እስከ 50 አዲስ ራእይ መጽሄቶችን መሸጥ ይጠበቅበታል።
ኢሳት ከመንግስት በኩል ማረጋጋጥ ባይቻልም ስለመለስ ዜናዊ ማንነት የምትተርከው አዲስ ራእይ መጽሄት በሚሊዮን  የሚቆጠር ቅጅ እንዲታተም መደረጉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል ። አንዳንድ ወገኖች የታተመው መጽሄት ቁጥር እስከ 6 ሚሊዮን ይደርሳል በማለት ለኢሳት ገልጸዋል።
መጽሄቱን ለማስተዋወቅ በቀረበው ማስታወቂያ ላይ ” ጀርመናዊው ፈላስፋ ዊልያም ፍሬዴሬክ ሄግል ” አለማዊ ምጡቅ የታሪክ ስብእና ከአፍሪካ አይፈልቅም” ሲል ከምእተ አመት በፊት የዘጋውን ድርሳን የከፈተው ኢትዮጵያዊው አፍሪካዊ መለስ ዜናዊ መሆኑን ያውቃሉን?” የሚል ተጽፎ ይገኛል።
ማስታወቂያው በማያያዝም ” ርእዮተ አለም ያልገደባቸው ታላላቆቹ  የአለም መሪዎች የማይሰለች፣ የሚመኩበት፣ የአዳዲስ እውቀቶች ቀዳሚ ተመጋቢ በማለት አሞካሽተውና ብሩህ አእምሮውን አድንቀው ሊጠግቡት ያልቻሉት በምን ምክንያት ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች ቱባ ምላሽ ያላት አዲስ ራእይ ብቻ ናት ” ሲል ገልጿል
በመጽሄቱ ግርጌ ላይ ”  ታጋይ መለስ ያዘጋጃት የነበረችው አዲስ ራእይ ተዝቆ ከማያልቀው የመለስ ስራዎች የቅምሻ ያህል እንካችሁ የምትለው እንደ ወትሮው ለኢህአዴግ አባላት ብቻ አይደለም፣ በመሪው ሞት ጥልቅ ምሬትና ድንጋጤ ፣ ሀዘንና ቁጭት ውስጥ ገብቶ መለስ ያወረሰንን እናሳካለን ብሎ ቃል ለገባው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።” በማለት መጽሄቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚሸጥ ኢህአዴግ ግልጽ አድርጓል።
አዲስ ራእይ መጽሄት ቀድሞ 10 ብር ይሸጥ ነበር። ልዩ እትሙ ደግሞ 100 ብር እየተሸጠ ነው። “ኢህአዴግ ህዝቡ የመለስን ታሪክ እንዲያውቅለት ቢፈልግ ኖሮ ዋጋውን  100 ብር ከማድረግ 10 ብር  ያደርገው ነበር፣ ኢህአዴግ በመለስ አስከሬን ቢዝነስ እየሰራ ነው፣ ንግድ ነው የያዘው”  በማለት አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ጋዜጠኛ ለኢሳት ገልጿል። ” 6 ሚሊዮን ቅጅ በመቶ ብር ከተሸጠ 600 ሚሊዮን ብር ይሆናል። ይህ አሀዝ ኢህአዴግ ለመለስ ለቅሶ ያወጣውን ዋጋ ሸፍኖ እጅግ በርካታ ትርፍ ያጋብስበታል፣ ፓርቲው በመለስ ስም  የኢትዮጵያን ህዝብ እየዘረፈ ነው፡ ” ሲል ጋዜጠኛው አክሏል ።
መጽሄቱን በግድ እንዲገዛ የተገደደ በጎንደር ከተማ የሚኖር ነጋዴ ደረሰኙ የብአዴን መሆኑንና “የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ድርጅትን ማጠናከሪያ የሚውል” የሚል አረፍተ ነገር እንዳለበት ተናግሯል።
በአዲስ ራእይ ስም የሚገኘው ገንዘብ ለአራቱ ድርጅቶች ሊካፈል እንደሚችል መረጃዎች ጠቁመዋል።  መጽሄቱን የሚያትመው የህወሀት ኩባንያ የሆነው ሜጋ አሳታሚ ድርጅት ነው። ህወሀት ለትግራይ ኮታ ከተመደበው ሽያጭ ብቻ ሳይሆን በሜጋ ማሳተሚያም በመጽሄቱ ሽያጭ ከፍተኛ ገንዘብ ያጋብሳል ተብሎ ይታመናል ።

    No comments:

    Post a Comment