ከበልጅግ ዓሊ
እስከ መቼ ነው ዝምታ? እስከ መቼ ነው አርምሞ ?
የልብን ሐቅ አስታሞ፣ የብእር አንደበት ለጉሞ፣
እስከመቼ ነው ዝሙ ? እስከ መቼ ነው አርምሞ??
“መቼን” የማታውቅ ልቤ ፣ አርምሞህን እነቀው፣
በል እባክህ እንዳቅምህ ፣ ባለችህ መንገድ አፍስሰው፣
እስከመቼ ነው አርምሞህ? ዝሙስ እስከመቼ ነው ??
ነሐሴ 1970 ,ፍቃደ አዘዘ
ሱዛን ራይስ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ ተወካይ ለጠቅላዩ ቀብር አዲስ አበባ በነበረችበት ወቅት ባደረገችው ንግግር መለስ ለሞኞችና ለደደቦች ትዕግስት አልነበረውም (Of course he had little patience for fools, or idiots, as he liked to call them.) ብላ ተናግራ ነበር። መለስ (fools, or idiots) ብሎ የሚጠራው ወዳጆቹን ሳይሆን ተቃዋሚውን ክፍል መሆኑ ይታወቃል።
መለስ በግል ጥቅም ምክንያት ባሰባሳባቸው ኮልኮሌዎች ወይም እንደ ሱዛን ዓይነት የሃገራቸውን ጥቅም ባስጠበቀላቸው የውጭ ዜጎች አካባቢ እንደ <<ምርጥ መሪ>> ይቆጠር እንደሆን እንጂ፣ በምንም መለኪያ አምባሳደሯ እንደካበችው ዓይነት እንዳልነበረ ቢያንስ የ97 ምርጫና ውጤቱን ለተከታተለ ግልጽ ነው።
ዛሬ የመለስ ራዕይ ተብሎ ሽብ እረብ የሚባልለት፣ ምርጫ ከማጭበርበር፣ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን በሽብርተኖች ስም ከማሰር፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ አካላትን ከማሳደድ፣ በሃይማኖት ውስጥ እየገባ ከማራበሽ ሊያልፍ አልቻለም። ለዚህ ነው የሱዛን ንግግር ለውሽት የቀረበ ተራ የካድሬ ፕሮፖጋንዳ እንጂ አደባባይ ላይ በግልጽ የሚታይ ክስተት ያልሆነው።
ምንም እንኳን የሱዛን ማጋነን ተራ ጭፍን ድጋፍ ቢሆንም ለእውነት የቀረበበት ጉዳይ የለበትም ማለት አይደለም። ተቃዋሚዎች በተለይ መሪዎቻቸው መለስ እንደ ጅልና ደደብ አድርጎ እንደቆጠራቸው አይደሉም ብሎ ለመከራከር እኔ በበኩሌ ድፍረት አይኖረኝም። ተቃዋሚዎች ብዙ ቢያስወግዷቸው ለድል የሚቀርቧቸውን፣ በሕዝብ ታማኝነት ሊያስገኙላቸው የሚችሉ ጠንካራ ጎኖቻቸውን በመተው፣ ለግል ታዋቂነት፣ ለሥልጠን ጉጉት፣ ለአንዳንድ ትናንንሽ ጥቅማ ጥቅሞች ሲሉ የሚያሰድባቸውን ደካማ ተግባራትን አይፈጽሙም ማለት ለውሸት የቀረበ ይሆናል።
የቅንጅት መሪዎች በተለይ ከ97 ምርጫ በኋላ ያገኙትን የሕዝብ ድጋፍ ወደ ጎን በመተው፣ በእንቶ ፈንቶ ጭቅጭቅ ተከፋፍለው፣ ሃገር ጥለው ወጥተው በሰሜን አሜሪካ ጡንቻቸውን ሲፈታተኑና ሕዝብን ተስፋ ሲያስቆርጡ ለተከታተለ ተመልካች እነዚህ ሰዎች እውነትም ጅሎች ናቸው እንዴ? ብሎ ቢጠይቅ ወይም ቢሳደብ ትክክል አይደለም ለማለት እንደፍር ይሆን? ከዛ በኋላስ ስንት ድርጅቶች ተራ ቅራኔዎችን ሰማይ አሳክለው ተከፋፍለዋል? ይህንን እያወቅን ብንደብቀውም የአደባባይ ምሥጢር ነውና ያጋልጠናል።
በዚህ ምክንያት የሱዛን ዘለፋን እንደ ስድብ ሳንወስደው<<በገንቢ ሂስነቱ>> ከተመለከትነው ለእውነት የቀረበ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም መለስ ይህንን ዘለፋ የተጠቀመው የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እንጂ የተቃዋሚዎችን ድክመት ለማረም እንዳልሆነ በሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸው ግፎች ደግሞ አጉልተው ያሳዩናል። ሱዛንም ይህንን በመደገፍ ለዴሞክራሲ ሳይሆን ለሃገሯ ጥቅም እንደቆመች ያጋልጣል።
በእውነት ለተመለከተው በተቃዋሚው ጎራ የሚሠሩ፣ ወይም የሚቀነቀኑ ብዙ ሊያሰድቡ የሚችሉ ተግዳሮቶች
በየወቅቱ እንመለከታለን። ተቃዋሚዎች በአንዳንድ ወቅት ከሕዝብ ድጋፍ የሚያገኙበትን ትተው በሕዝብ የተወገዘውን አንስተው መርህ መፈክራቸው አድርገው ሲነጉዱ ይታያሉ። ታዲያ ይህንን ልብ ብሎ ለተመለከተ እነዚህ ተቃዋሚዎች ሞኝ ናቸው? ብሎ ቢጠይቅ ምን ይደንቃል?
የሕዝብን ድጋፍ በመመልከት እነመለስ ሰንደቅ ዓላማችንን <<ጨርቅ>> ነው ማለት እንዳላዋጣቸው ሲያውቁ በዚያ አልቀጠሉም። እንዲያውም አልፈው ተርፈው የሕዝብ ድጋፍን ለማግኘት የማያምኑበትን ሰንደቅ ዓላማ አፍቃሪ ሆነው በእሱ ተጠቅልላው እስከመቀበር ደረሱ እንጂ። ወያኔ ይህንን የፖለቲካ ቁማር ሲጫወት አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ ሰንደቅ ዓላማውን በመሸሽ ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ የዘር ፖለቲካን በማጉላት የተለያዩ የጎጥ ሰንደቅ ዓላማዎች ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት፣ ብሎም ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚያወራውን እስከ ማውገዝ የተደረሰበት ሁኔታ እያየነው ነው።
ይህ የተለያየ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ <<እኛ ከወያኔ የበለጠ ዘረኞች ነን>> የሚለው መፈክር አንግቦ መጓዝ ከግል የሥልጣን ፍላጎት አንጻር የተተለመ እንጂ የሕዝብ ፍላጎት ያላካተተ መሆኑን በ21 ዓመት የተቃዋሚዎች ንቅናቄ አለመረዳት ቢያሰድብ ሊገርመን አይገባም። የሕዝብ ፍላጎትን ባለማጤን፣ የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያገናዝቡ የሚታለም ትግል የት ሊያደረስ እንደሚችል የታወቀ ነው። ግልጽ ለማድረግ የግልን ኪስ ያዳብር እንደሆን እንጂ ወያኔን በተጨባጭ መቃወም የሚችል አማራጭ አይሆንም። በሕዝብ ዘንድም ተቀባይነት አያገኝም። የዘር ፖለቲካን ከወያኔ በላይ እናስፈጽማለን ብለው የሚባዝቱ የተቃዋሚነት ትግሉን ትተው ወያኔን መደባለቅ እንደ ብልህ ያስቆጥራቸዋል።
ወያኔ የዓባይ ግድብ እያለ የኢትዮጵያዊነት ራዕይ አለኝ በሚልበት ወቅትና በዛ ስም ለመነገድ ጥረት ሲያደርግ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ የእከሌ ነጻ አውጭ ፣ የዚህ ዘር ነጻ አውጭ በሚል በሚጓዙበት ወቅት ላይ ደርሰናል።ከወያኔ በኋላ የሚመጣው መንግሥት በዘር ላይ የተመሰረተ ይሆናል ብለው የሚያምኑ ካሉ ሱዛን ከመለስ ነው ብላ የወሰደችው ስድብ ትክክል ነው ማለት ነው።
በጀርመን ቋንቋ 1982 የዓመቱ ምርጥ ቃል ተብሎ የተመረጠ ቃል አለ።ይኸውም (Ellbogengesellschaft) የሚል ነው። ቃሉ የመሠረተው ከሁለት ቃላት ነው። Ellbogen – ክርን፣ ጡጫ ማለት ሲሆን gesellschaft- ማህበረሰብ ማለት ነው። በአጠቃለይ ቃሉ በሕብረተሰብ ውስጥ በግል ለመታወቅ ወይንም የግል ታዋቂነትን በመሻት(Egoismus) በመፈለግ የሚደረግን የእርስ በእርስ ትግል ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ነው። በእንግሊዘኛ (everyone-for-himself- dog-eat-dog society) የሚለው ይሆናል። ይህ አገላለጽ በአሁኑ ወቅት በተቃዋሚው ጎራ እየሰፋ የመጣውን የመከፋፈል ፖለቲካን በደንብ ይገልጸዋል።
ወያኔ የትግራይ ነጻ አውጭን የሚለው ስሙ ስላልጠቀመው በኢሕአዴግ ስም አንድ ሆኖ ለመታየት ሲጥር ተቃዋሚዎች ደግሞ አዲስ በተፈጠረው “የዴ“ ፖለቲካ ራሳቸውን እየከፋፈሉ የሕዝብ ፍላጎትን ሲጋፉ ለተመለከተ “ኢዲየትስ” ቢላቸው ሊጨንቀን አይገባም።
<<የዴ ፖለቲካ>> ከመከፋፈል አንጻር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የቆየ ቢሆንም በዚህ ዓይነት መልኩ ግን አዲስ የተፈጠረ ነው። ይህ አዲስ የክፍፍል ፖለቲካ በተለያየ ምክንያት ይምጣ እንጂ ትግሉን በጣም የጎዳ ነው። ድርጅት ሲከፋፈል ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ከቅንጅትና ከኢሕአፓ መማር ይቻላል። የእህል ናዳ ሲቃጠል ሞኝ ይስቃል ፣ ብልጥ ያለቅሳል እንዲሉ በክፍፍል ወደ ሥልጣን የቀረቡ እየመሰላቸው ጮቤ የሚረግጡ እንደሞኝ ቢቆጠሩ ሊገርመን አይገባም። ከሁሉ የሚያሰድበው ደግሞ የድርጅት ምስጢር የአደባባይ ወሬ ሲሆን ነው። በተለይም ደግሞ ይህ ክፍፍል(እንደ ዓይጋ ፎረም ) ዓይነት የጠላት መድረክ ላይ ሲሆን ምንኛ ያስጠላል? አብረው የተገበሩትን ጉዳይ ሲጣሉ እርስ በእርስ መገላለጥ ያላሰደበ ምን ያሰድብ? የወያኔ ደጋፊዎች ይህንን እየተመለከቱ እነዚህ “ኢዲየትስ” ቢሉ ሊገርመን አይገባም።
በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ይህ የመከፋፈል አዝማሚያ ሲጀምር አብሮ የሚጀምረው የክፍፍሉ መሪዎች ብዙሃኑ እኔን ነው የሚደግፈው የሚለው ይሆናል። ይህ ሞኝነት ነው። ታሪክ ግን ያስተማረን ሌላ ነው። ብዙሃኑ በክፍፍሉ ተስፋ ቆርጦ ትግሉን ነው የሚያቆርጠው ወይም ዝምታን የሚመርጠው ነው። መሪዎች የሚከራከሩበት ብዙሃን ሊሆን የሚችለው ከደሃጣኑ ላይ ነው። ይህንን በቅንጅት አይተነዋል። ግንቦት ሰባትም ይሆን መኢአድ ቢደመሩ የቅንጅትን ዓይነት ኃይል አይኖራቸውም ። ኢሕአፓና ኢሕአፓዴም ከመከፋፈላቸው በፊት የነበረውን ኃይል አለን ብለው መዋሸት አይችሉም ። ግንቦት ሰባትና ዴውም እንደዚሁ። ሕዝብ ወይም አባላት የሚፈልጉት አንድነታቸውን ሲሆን መከፋፈላቸውን የሚቀነቅኑትን ጅሎች ቢባሉ ሊከፋን ነው ማለት ነው?
በሌላ ደግሞ እንመልከት ለደቂቃ ታክል የአሁኑ መሪ መፈክራችን ምንድነው? ብለን እንጠይቅ። መልሱ ቀላል ነው። <<አዜብ ከቤተመንግሥት ትውጣ>>?ከቤተመንግሥት ለማውጣት ነው ወይ የምንታገለው? ብለን ብናስብ መልሱ ቀላል ነው። የተነሳንበት ዓላማ የኢትዮጵያ አንድነት እንጂ የአንዲት እንስት የቤተመንግሥት የቤት ኪራይ ጉዳይ አይደለም። አሁንም ቢሆን ከልደታም ሆነ ከቄራ ፣ ከጨርቆስም ይሆን ከቦሌ ይህንን መንግሥት እስከ መራች ድረስ ቤተመንግሥት መኖር አለመኖሯ ልዩነት አያመጣም። ግን ተቃዋሚዎች የአዜብ የቤት ኪራይ ጉዳይ እንደ ወሳኝ ጥያቄ በሚስተዳድሯቸው የመገናኛ ዘዴዎች ሲቀነቅኑ መስማት ደግሞ ለምንድነው የምንታገልው ? እውነትም “ ኢዲየትስ “ ነን እንዴ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ተቃዋሚዎች የሚሰባስባቸውን አንድ መሪ መፈክር ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ የመሪን መፈክር በወቅታዊ መፈክር መቀየር በተከታታይ የታየ የተቃዋሚዎች ድክመት ነው።