Thursday, December 6, 2012

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የብሄር ብሄረሰቦችን በአል አከባበር ነቀፉ


 ኢሳት ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የብሄር ብሄረሰቦች በአል አከባበር  የይምሰል ነው በማለት ተችተዋል።  የተረፈች ልጅ በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስድስት ኪሎ ግቢ ተማሪ እንደተናገረው ኢትዮጵያ በጥቂቶች የምትገዛ ፣ አብዛኛው ህዝብ የበይ ተመልካች የሆነባት አገር ናት ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የብሄሮች መብት አለመከበሩ በግልጽ የሚታየው በስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው የሚለው ተማሪ፣ ተማሪዎች እርስ  በዘር በመከፋፈላቸው ለመገናኘትና በአንድ አገር ጥላ ስር ለመቆም እየከበደ መምጣቱን ተናግሯል ።
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ኢህአዴግ ያስገኘው የብሄር ብሄረሰቦች መብት ውጤት ተደርጎ እየታየነው ምን አስተያየት አለህ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ሀይለማርያም ማለት ” የራሺያው ሜድቬደቭ  ነው፣ ስልጣን የለውም ለምልክት የተቀመጠ ነው” በማለት መልሷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  የተንሰራፋው ዘረኝነት ተማሪዎች ለአገራቸው ጉዳይ በአንድነት እንዳይቆሙና እንዳይታገሉ  እንዳደረጋቸው ተማሪው ገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ በዛሬው እለት በአዋሳ ዩኒቨርስቲ የብሄር ብሄረሰቦችን በአል ያከበረ ወጣት እንደገለጠው በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄረሰቦች መብት ተከብሮአል ብሎ እንደማያስብ ገልጿል።
የአንድነት ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆነው ወጣቱ ፖለቲከኛ ዳዊት አስራደ በበኩሉ ህገመንግስቱ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት መከበር እንደሚደነግግ ገልጾ፣ ይሁን እንጅ በህገመንግስቱ ውስጥ የሰፈሩት መብቶች ባለመከበራቸው የብሄሮች መብት ተከብሯል ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጿል።
ክልሎች ራሳቸውን እያስተዳደሩ ነው ብሎ እንደማያምን የገለጠው ወጣት ዳዊት፣ በብሄር ደረጃ መብቱ የተከበረለት ብሄር አለመኖሩን  ይሁን እንጅ የገዢው ፓርቲ ሰዎች የሰዎችን መብት እስከ መድፈር የሚደርስ መብት እንደተከበረላቸው ገልጿል( 7፡08-7፡35)። በብሄሮች ጥያቄ ላይ ያቀናበርነውን በነገው እለት በትኩረት ዝግጅት ላይ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ በመያዝ በአሉን እንዲያከብሩ እየተገደዱ መሆኑን ርእሰ መምህራን ለኢሳት ገልጸዋል። አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገ ርእሰ መምህር ” ትምህርት ቤቶች የኢህአዴግ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ሆነዋል” ሲል ገልጿል።
ተማሪዎች ሳምንቱን ሙሉ በአል አክብሩ በመባላቸው የትምህርት ሂደቱ እየተስተጓጓለ መምጣቱን መምህሩ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment