June 22, 2013
አቶ ገብረመድህን አርአያ*
ከአውስትራሊያ
ከአውስትራሊያ
ወደ ግንቦት 20ቀን, 1983 ዓ.ም. ከመግባታችን በፊት ትንሽ ወደ ኋላ መለስ በማለት የደርግ ስርዓትን በትንሹ እንቃኘው::
ደርግ
የካቲት ወር 1966 ዓ.ም. የዘውድ አገዛዙን ስርዓት በመቃወም በአርሶ አደሩ ፣ በተማሪው ፣ በአስተማሪው ፣ በመንግስት ሰራተኛው ፣ በወዛደሩ ፣ በነጋዴው እና በመለዮ ለባሹ ወዘተ ፣ ወዘተ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ጊዜ ሳይወስድበት በ6 ወራት ውስጥ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ ግቡን መታ::
ህዝባዊ አመጹን የሚመራው የተደረጀ ፓርቲ ባለመኖሩ በር የተከፈተለት መለዮ ለባሽ አመቺ ሁኔታ በማግኘቱ በፍጥነት ተደራጅቶ ከተራ ወታደር ጀምሮ የተለያዩ ማእረግ ያላቸው አባላቱን አስመርጦ ወደ 120 የሚጠጉ ተወካዮቹን አዲስ አበባ በሚገኘው አራተኛ ክፍለጦር አሰባሰበ::
ከጦር ሃይሎች ፣ ከክቡር ዘበኛ እና ከፖሊስ የተውጣጡት እንኚሁ መለዮ ለባሾች በሰኔ ወር 1966 ዓ.ም. ተሰብስበው ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መስርተው “ኢትዮጵያ ትቅደም ፣ አቆርቋዥ ይውደም” በሚል መርህ ስር ሰፊ ሊባል የሚችል የህዝብ ድጋፍም አግኝተው ነበር::
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. የተመሰረተው አስተባባሪ ኮሚቴ ንጉሱን ከስልጣን አውርዶ “ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” የሚል ስም በመያዝ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ጀመረ:: ቀስ በቀስም ደርግ የስልጣን ወንበሩን በማመቻቸት የሃገሪቷ መንግስት ለመሆን ቻለ::
በወቅቱ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሃገራት ሶሻሊዝም ወይም ህብረተሰባዊነት በሚባል ርዕዮተ አለም እድገት እና ብልጽግና የማይገኝበት “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” ስርዓት በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና ቻይና ፕሮፖጋንዳ አለምን እንደማዕበል ሲወዘውዛት የነበረበው ሁኔታ ሆኖ በደርግ የተመሰረተው መንግስት ግራና ቀኙን ሳይመለከት ሶሻሊዝም በኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈጥረውን ቀውስ እና ችግር ሳያጤን እና ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን ሳያማክር በ1972 ዓ.ም. ኢሰፓአኮን(የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን) መሰረተ:: ይህንን ምስረታ ተከትሎም ደርግ አንድ እግሩን ገደል ከተተው::
በዚህ ጽሁፍ ሁለት ነገሮችን ለያይቼ በማሳየት ለማለፍ እሞክራለሁኝ፤
1) ደርግ እንደ ፖለቲካ ተቋም እና ስርዓት
2) መለዮ ለባሹ እንደ አገር መከላከያ ሰራዊት
ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያዊ የሆነ እና በዘመናዊነቱ በአፍሪካ ጭምር ተወዳዳሪ ያልነበረው እንደነበር ነው:: የደርግ ስርዓት ከወታደሩ በወጡ ሰዎች ቢመሰረትም ሰራዊቱ ግን በየትኛውም መለኪያ የኢትዮጵያ ሰራዊት ለመሆኑ ከጥያቄ ውስጥ ሊያስግባው የሚችል አንዳችም መከራከሪያ ሊቀርብ አይችልም:: አገራችን ዘመናዊ ጦር ማደረጀት ከጀመረችበት ከሃያኛው ክፍለዘመን መባቻ ጀምሮ በስንት ወጪ እና ጥረት የገነባችውን ጦር የ “ደርግ ጦር” የሚል ቅጽል በመስጠት ከፍተኛ የሆነ የስም እና የሞራል ማጥፋት ዘመቻ የፈጸሙበት ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑት ወያኔ እና ሻዕቢያ ናቸው::
ይህ ጦር ደሙን አፍስሶ ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፤ ራበኝ ፣ ደክመኝ ሳይል ወያኔ እና ሻዕቢያን እግር እግራቸውን እየተከታተለ ሲደመሥሳቸው እና ሲያጠፋቸው የነበረ የኢትዮጵያ ብርቅ ልጅ ነው:: የዛሬው የወያኔ ዘረኛ ሰራዊት ግን እንኳን ስለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሊከላከል ይቅርና ራሱ የወያኔ ሰራዊት ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ህዝብ የአንድ ጎጠኛና ዘረኛ ታጣቂ ቡድን ነው:: አሁን ያለው በዘር የተደራጀው ቅጥረኛ እና ባንዳ ሰራዊት በየትኛውም መለኪያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተብሎ ሊወሰድ የሚችልበት ሁኔታ የለም::
የደርግ መንግስት በስልጣን በቆየበት 17 አመት ውስጥ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ቀይ ባህርን የጠበቀ ፤ ከገንጣይ እና አስገንጣዮች አገሪቷን እየተከላከለ ሉዓላዊነትን የጠበቀ የኢትዮጵያ ስርዓት ነበር::
በሚከተለው ርዕዮተ አለም ቀስ በቀስ እየተዳከመ በመሄድ እንደነበረው አገርና ህዝብ ለማዳን አልቻለም:: ደርግ በተዳከመ ጊዜም ሰራዊቱ ይዳከማል:: አንድ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከመንግስት የሚቀርብለት ነገሮች ብዙ ናቸው:: ይህ አልሆነም:: ሰራዊቱም መንግስት በመዳከሙ ምክንያት የነበረው አልበገር ባይነት ስሜቱ እና ጀግንነቱ የውጊያ ብቃቱ ተስፋ በመቁረጡ ችግር እየፈጠረለት ሄደ ቢሆንም ግን ወያኔም ሆነ ሻዕቢያ አሁንም ፈቀቅ ሊሉ አልቻሉም:: የማይበገር የኢትዮጵያ ሰራዊት መሆኑን ያውቁታል እና::
ይህ በዚሁ እንዳለ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት መንግስቱ ሃይለማሪያም ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ለቀው ዚምባብዌ ሃራሬ ገቡ:: እዛም ጥገኝነት ጠየቁ:: መሆን የማይገባውን ስራ ሰሩ:: በኢትዮጵያ ሃገራቸው ሰርተው ሂወታቸው ቢያልፍ ታላቅ ስምና ክብር ያገኙ ነበር:: ግን አላደረጉትም:: ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሰራዊት ተበተነ::
ግንቦት 15 ቀን 1983 ዓ.ም. በፕሬዚደንት መንግስቱ እግር የተተኩት ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን በዜና እወጃ የኢትዮጵያ ሰራዊት የነበርከው በያለህበት ቦታ መሳሪያህን ለህወሃት(ኢህአዴግ) እና ለሻዕቢያ እያስረከብክ ወደ ምትፈልግበት ሂድ፤ ሻዕቢያም ኤርትራን ህወሃትም ኢትዮጵያን እንዲቆጣጠሩ ፈቅደናል በማለት ፍጹም ክህደት በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ እና ህዝብዋን ለደመኛ ጠላቶች አሳልፈው ሰጡ::