የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በሞት ከተለዩ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በየመድረኩና
በመንግስት መገናኛ ብዙሃን “የመለስን ራዕይ እናሳካለን” በሚል የሚነገረው ፕሮፖጋንዳ እጅግ የበዛና አሰልቺ
እንደሆነባቸው ያነጋገርናቸው አንዳንድ የአ/አ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ያሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ወሬያቸው ሁሉ በመለስ ራዕይ ማሳካት ጋር
የተያያዘ ከመሆኑም ባሻገር አቀራረቡም ሆነ የድግግሞሹ ብዛት አድማጭና ተመልካቹን የሚያሰለች መሆኑን አንድ
አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል፡፡
የትኛውም ዓይነት ስብሰባዎችን ለአቶ መለስ ጸሎት በማድረግ መጀመር የግድ እየሆነ መምጣቱን የጠቀሰው አስተያየት
ሰጪያችን በአዲስ አበባ አስተዳደር በአንዳንድ መ/ቤቶች ደብዳቤ መጻጻፊያ ማሳረጊያ ላይ “ከሰላምታ ጋር” በሚለው
የመልካም ምኞት መግለጫ ምትክ “የመለስ ራዕይ ይሳካል!” በሚል መጻፍ መጀመሩ ነገሩ የቱን ያህል ግለሰብ
ወደማምለክ ደረጃ መውረዱን የሚያሳይ ተጨባጭ ምሳሌ ነው ብለዋል፡፡
አቶ መለስን ማምለኩ መቼ እንደሚያቆምም አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየጎዳናውና በመንግሰት መ/ቤቶች አቶ መለስን የሚያሞግሱ መፈክሮችን የመስቀሉ ሥራም
ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆሙት ሌላው የአ/አ ነዋሪ ቀጣዩን የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ በሞተ ሰው ራዕይ ለማስቀጠል ሌት
ተቀን የሚደረገው ውትወታ ከፍተኛ አመራሩ ለምን የሙጢኝ እንዳለ ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡
በአሁን ሰዓት ኢህአዴግ የሚባለው ግንባር በአቶ መለስ ራዕይ ሙሉ በሙሉ መተካቱ ለግንባሩ ውድቀት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment