Monday, December 17, 2012

ከፍተኛው ፍርድቤት በሙስሊም መሪዎች ላይ ብይን ሰጠ


የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ አቶ አቡበክር የክስ መዝገብ በሽብረተኝነት ወንጀል በተከሰሱት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ  ብይን ሰጥተዋል።
ችሎቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ እና ታሳሪዎች ወደ ማረሚያ ቤት እስኪመለሱ ድረስ ከልደታ እሰከ ኮካ ኮላ ድረስ ያለው አካባቢ በመላ በፌደራል ፖሊስ ተወጥሮ ነበር።
ፍርድ ቤቱ ከቀረቡት ክሶች ውስጥ መንግስትን የመገልበጥ ሙከራ የሚለውን ሁለተኛውን ክስ ውድቅ አድርጎታል። ከአንደኛው ክስ ላይ ደግሞ የሽብር ፈጠራ ከሚለው ላይ ሙከራ ፣ ማነሳሳት የሚለውን አንቀጽ 4 ወጥቶ በአንቀጽ 3 ድርጅቱን በራስ ማድረግ የሚለው ላይ እንዲጠቃለል ወስኗል።
23ኛን ተከሳሽ  በሚመለከት የአእምሮ ህመምተኛ በመሆኑ ተነጥሎ እንዲታይ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላልፎ፣  ከአማኑኤል ሆስፒታል የምርመራ ውጤት እንዲመጣለት አዟል። ነገር ግን ተከሳሹ በዋስትና ወጥቶ እንዲከራከር ጠበቆች ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል።
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን ክሱን ይከላከሉ ሲል ብይን በማስተላለፉ ከጥር 14 ፣ ቀን 2005 ዓም ጀምሮ ለተከታተይ 10 የስራ ቀናት የአቃቢ ህግ ምስክሮች ቀርበው በተከሳሾች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ውሳኔ አሳልፎአል።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት የአቃቢ ህግ ክስን፣ የጠበቆችን መቃወሚያ እና የአቃ ህግ የመቃወሚያ መቃወሚያ ሀተታ በንባብ የሰማ ሲሆን፣ ጠበቆቹ የጸረ ሽብር አዋጁ የህግ ትርጉም ስለሚያሻው ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ይሂድ የሚለውን ፣ የአቶ ጁነዲን ሳዶ ሚስት ክስ ተነጥሎ ለብቻው መታየት አለበት ፣ ፍርድ ቤቱ ይህን ክስ የማየት ስልጣን እንደሌለው እና ክሱ መሰረት ስለሌለው ሊዘጋ ይገባል የሚለውን አቤቱታ አልተቀበለውም። የህገመንግስት ትርጉም ፍርድ ቤት ሲያምንበት ብቻ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሚልከው ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃላቸውን የጠየቃቸው ሲሆን እነሱም ህገመንግስታዊ መብታችንን ከመጠየቅ ውጭ ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምንም፣ መብታችንን በሰላማዊ መንገድ መጠየቃችን ወንጀል ሆኖ ነው ያሳሰረን ያሉ ሲሆን ፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው በበኩሉ ምንም ወንጀል አልሰራሁም ነገር ግን በእኔ ላይ ወንጀል ተፈጽሞብኛል ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተለያዩ መስጊዶች በገንዘብና በጥቅማጥቅም የተመለመሉ የአቃቢ ህግ ምስክሮች  በአቃቢያን ህግ እና መርማሪ ፖሊሶች ድጋፍ የምስክርነት ስልጠና እና የተግባር ልምምድ በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment