በሶማሊ ክልል በጅጅጋ ከተማ ተወልደው ያደጉ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት በአማራ ክልል በመገኘት የብሄር ብሄረሰቦችን በአል አክብረው በተመለሱ ማግስት የንግድ ድርጅቶቻችሁን አስረክቡ እንደተባሉ ገልጸዋል።
ቀደም ብሎ ታይዋን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የልብስ እና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጥ ሱቆችን ከፍተው ሲሰሩ የነበሩ ነጋዴዎች እንደገለጹት፣ መንግስት ሱቆቻቸውን እንዲያስረክቡ ያደረጋቸው ፣ የሌሎች አካባቢ ተወላጆች የንግድ ድርጅቶችን በብዛት ይዘዋል በሚል ምክንያት ለክልሉ ተወላጆች ለማስረከብ ነው። የሌላ አካባቢ ተወላጆች ብቻ በመሆናችን ጉልበታችንንና ገንዘባችንን አፍስሰን ያለማነውን ቦታ ተቀምተናል በማለት ነጋዴዎች ተናግረዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ በጅጅጋ ተወላጅ የሆነ የመንግስት ሰራተኛም በጅጅጋ እየተፈጸመ ያለው ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ተናግሯል::
በክልሉ የሚኖር ሌላ ኢትዮጵያዊም እንዲሁ ከመሀል አገር የመጣ ወይም ዘመዶቹ ከመሀል አገር መጥተው በክልሉ የተወለዱ ሰዎች ምንም መብት የላቸውም ብሎአል ::
በሶማሊ ክልል የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እየከፋ ቢመጣም የፌደራሉ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ አልቻለም። አንዳንድ ነዋሪዎች ክልሉ ከፌደራል መንግስቱ እጅ እየወጣ ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
አንድንድ ወገኖች የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በመሀል አገር ተወላጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በሶማሊ ተወላጆች ላይም የሚፈጸም ነው።
የሶማሊ ተወላጆች በሚፈጸምባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅትን በብዛት እየተቀላቀሉ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
No comments:
Post a Comment