Tuesday, January 1, 2013

የማፍረስ አባዜ


በአለፉት ሃያ አንድ ዓመታት፣ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ፣ የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ልዩ መታወቂያው ያደረገው እያፈረሱ መገንባትን ነው፤ ማፍረስ ቀላል ሥራ ነው፤ ጭንቅላትም፣ ማሰብም አይጠይቅም፤ ልብም፣ ስሜትም አይጠይቅም፤ የሚጠይቀው የዝሆን አካልና ጉልበት ብቻ ነው፤ አንድ ቤተሰብ ስንት ዓመት በዚያ ቤት ውስጥ ኖረ? ጎረቤቶች ምን ዓይነት ትስስር አላቸው? በማኅበር፣ በእድር፣ በዝምድና በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤተ መስጊድ፣ በመቃብር፣ በሥራ፣ በአጠቃላይ የእያንዳንዱ ሰው ኑሮ ከልደት ጀምሮ የተፈተለበትና የተደራበት ውስብስብ የኅብረተሰብ አካል መኖሪያ ነው፤ ይህንን አካል ለማፍረስ ትንሽ ጭንቅላትና ግዙፍ ጡንቻ ያለው አይቸግረውም፡፡
መኖሪያ ቤቶችን ማፍረስ፣ መቃብሮችን ማፍረስ፣ የንግድ ድርጅቶችን ማፍረስ፣ ትምህርት ቤቶችን ማፍረስ፣ … ማፍረስ… ማፍረስ… ማፍረስ! ሳያለቅሱ እያስለቀሱ ማፍረስ፤ መሬቱን ማራቆት፣ ሰዎቹን ማራቆት፤ እያፈረሱ ማራቆት፤ እያራቆቱ ማስለቀስ፤ እያስለቀሱ ማፈናቀል፤ እያፈናቀሉ መጣል፤ የሚፈርሰው ቤት ብቻ አይደለም፤ የሚራቆተው መሬት ብቻ አይደለም፤ የሚፈርሰው ሰው ነው፤ የሚፈርሰው ከልደት ጀምሮ የነበረ ጉርብትና ነው፤ የሚፈርሰው ለዘመናት የተገነባ ዝምድና ነው፤ የሚፈርሰው የኑሮ የመደጋገፍ ተስፋ ነው፤ የሚፈርሰው የ‹‹ቀባሪ አታሳጣኝ!›› ጸሎት ነው፤ የሚፈርሰው የአጥቢያና የእድር የቀብር ዋስትና ነው፤ የሚበጣጠሰው ለብዙ ዘመናት የቆየ፣ በደስታና በሐዘን፣ በሳቅና በለቅሶ ማኅበረሰቡን ያስተሳሰረው ገመድ ነው፤ ይህ ለዘለዓለም ጠፍቶ የሚቀር፣ ማንም በምንም የማይተካው ማኅበረሰባዊ ክስረት ነው፤ የትውልድ መቋረጥ ነው፤ የታሪክ መቋረጥ ነው፤ የማይሽር የዜግነት ቁስል ነው፤ ከዜግነት የአገር ባለቤትነት ወደባይተዋርነት፣ ከሰውነት ወደኢምንትነት፣ ወደገለባነት መውረድ ነው፤ መዋረድ ነው፤ የተወለዱበትና ያደጉበት በጉልበተኞች ሲፈርስ አቅመ-ቢስ ሆኖ መፈናቀል፣ አገሬ ነው ባሉት ቦታ ባይተዋር ሆኖ መሰደድ ነው፤ በሌላ አገር ተሰድዶ ሁለተኛ ዜጋ መሆንን የሚመርጡ ሞልተዋል፤ ያውም ከተገኘ!ይህ ሁሉ ሀሳብ-የለሽ ማፍረስ የሚካሄደው በደሀዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ነው፤ ይህ ሁሉ ሀሳብ-የለሽ ማፍረስ የሚካሄደው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተዘረዘሩ መብቶች በአሏቸው ሰዎች ላይ ነው፤ በብዙ የዓለም-አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች የታወቁ መብቶች በአሏቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡
የማፍረሱን አባዜ ክፋቱን ገልጦ የሚያሳየው አንደኛ አብዛኛውን ጊዜ በክረምት መሆኑ ነው፤ ሁለተኛ ቤታቸው ለሚፈርስባቸው ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ እንኳን ሳይመቻችላቸው ሴቶችና ወንዶች፣ ሕጻናትና ልጆች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች፣ ሕመምተኞችና ደካሞች ሜዳ ላይ መውደቃቸው ነው፤ በኢጣልያ ወረራ ጊዜ ያየሁትን እየመረረኝ ልናገር፤ ኢጣልያኖቹ ደህና ደህና ቤቶችን ለሹማምንት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን መጀመሪያ ለባለቤቶቹ በመርካቶ ኢንዲጂኖ (የአገሩ ሰው ገበያ) የጭቃ ቤቶች ሠርተው ያስገቧቸው ነበር፤ ባለቤቶቹን ከቤታቸው የሚያስወጡት ወደአዲሶቹ ቤቶቻቸው ካስገቡ በኋላ ነበር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ የሚል ከወራሪ የፋሺስት ቄሳራዊ አገዛዝ እንዴት የባሰ መስሎ ይገኛል?
ለመሆኑ እነዚህ ቤቶቻቸው የሚፈርሱባቸው ሰዎች ኢሕአዴግን ከመረጡት 99.7 ከመቶ ውስጥ ያሉ ናቸው ወይስ ከዚያ ውጭ ያሉትና ያልመረጡት እየተፈለጉ ነው?
ቤት አፍራሾቹ ጊዜ የፈቀደላቸው ዘመናዮች ናቸው፤ በእነሱ ጭንቅላት ጊዜ ጸጥ ብሎ የቆመና በእነሱ ጡንቻ ብቻ የሚነጋና የሚመሽ ነው፤ ትዕቢት የሚባለው ይህ ነው፡፡
ቤቶቻቸው፣ የዘመዶቻቸው መቃብሮች፣ የንግድ ድርጅቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች ተራ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው፤ ለእነሱ ዓለም ተደርምሶ ለእነሱም ጊዜ ጸጥ ብሎ ቆሞአል፤ ትናንት ያለፉበት ሁሉ በጨለማ ተውጦአል፤ ትውስታም አልተወላቸውም፤ ነገ በጥላቻና በመረረ ቂም ተጋርዶ ንጋትን አያስመኝም፤ ቢጮሁ ድምጻቸው የማይሰማ፣ አቤት ብለው የሚጮሁበት መድረክ የሌላቸው፣ የእገሌ ያለህ! ወይም በእገሌ አምላክ! የሚሉት የሌላቸው፣ ቀኑ የጨለመባቸው ሰዎች ናቸው፤ አምላካቸው ብቻ ያያቸዋል፤ እንባቸውንም ይሰፍራል፤ ቀኑ ሲደርስም ያስከፍላል፤ የብርዱን ግርፋት፣ የጸሐዩን ጥብሳት፣ ረሀቡንና ጥማቱን ጉልበተኞቹ፣ ትዕቢተኞቹ ባያዩም እግዚአብሔር ያያል፤ አይቶም ይመዘግባል፤ መዝግቦም ዋጋ ያስከፍላል፤ ታሪክም መዝግቦ ለነገው ትውልድ ያስተላልፋል፤ ያፈረሱ የሚፈርሱበትን፣ ያራቆቱ የሚራቆቱበትን፣ ያዋረዱ የሚዋረዱበትን ቀን እግዚአብሔር ያመጣዋል፤ ያኔ ሁሉም እኩል የአገሩ ባለቤት ይሆናል፤ አፍራሽ ጉልበተኛ በሕግ ይታሰራል፤ ደካማውም ደሀ በነጻነት ጉልበትን ያገኛል፡፡
በቅርቡ ደግሞ ሌላ ዓይነት የማፍረስ ተግባር መጀመሩ ይሰማል፤ ዙሪያውን እየተቆፈረ ስለሆነ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ቢፈርስስ? የአጼ ምኒልክ ሐውልት ቢፈርስስ? ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢፈርስስ? ማን ይመክትላቸዋል? እንደ እንግሊዝ፣ እንደ ቤልጂክና እንደሩስያ ኤምባሲዎች ያለ የሚመክት ኃይል በአካባቢው የለም፤ በአንዳንድ አገሮች ለምሳሌ በእንግሊዝ አገር እንኳን ብሔራዊ ታሪክንና ስሜትን ያዘለ ሐውልትና ጥሩ የእርሻ መሬትም ለመንገድ እንዲውል ሕዝቡ አይፈቅድም፤ የሕዝብ ድምጽ ዋጋ ባለው አገር፡፡
ደሞስ እንኳን ሐውልትና አርበኞችን፣ ለአገራቸው ለወገናቸው፣ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የቆሰሉትንና የደሙትን፣ ስቃያቸውን ያዩትን ገድለናቸው የለም እንዴ? ሰቅለናቸው የለም እንዴ? በጥይት ደብድበናቸው የለም እንዴ? ባንዳዎቹ አርበኞቹን እየገደሉ ጨርሰው የባንዳዎቹ ልጆች የሚገድሉት አርበኛ ሲያጡ ሐውልት ቢያፈርሱ፣ ወይም የአሉላን ሐውልት ለሌላ፣ የሙሉጌታ ቡሊን መታሰቢያ ለሌላ ቢያደላድሉ አዲሱ ነገር ምንድን ነው? መካብ ሲያቅት ማፍረስ ሥራ ይሆናል፤ ወይም የማፍረስ አባዜ ከያዘ ካላፈረሱ መካብ የማይቻል ይሆናል፡፡
እግዚአብሔርም ያፈርሳል፤ ‹‹ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡›› ማቴ. 7/27

No comments:

Post a Comment