መግቢያ
የዳውሮ ሕዝብ የደረሰበትን የመልካም አስተዳደር እጦት፤ በአቅራቢያው ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት አለመቻል፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሕዝቡ ለሚያቀርበው የመብት
የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ያለመስጠት፤ በየወቅቱ በሚፈራረቁ የሥልጣን ተረኛ በሆኑት የህወሐት/ ደኢህዴን ካድሬዎች የግል ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ የወረዳ ማዕከል እየተወሰነ ከመንደር ወደ መንደር በመዘዋወሩ የተነሳ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት አለመቻል አበሳጭቶት ወደ አምጽ ማምራቱን በመዘርዘር ከዚህ በፊት በሦስት ክፍሎች ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ ማስነበቤ ይታወሳል።
አሁንም በሕወሃት/ ደህዴን ካድሬዎች ተንኳሽነት የተነሳ የሕዝቡ ቁጣ እንደገና እያገረሸ መጥቷል። እስሩ ማንገላታቱ ከሥራ ማባረሩ ተጀምሯል። የሕዝቡ ጥያቄ የሚታወቅና ግልጽ ነው። ከሚዲያና ከካድሬዎች የሚነገረውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ የልማትና እድገት ፕሮፓጋንዳ ባሻገር ድርሻውን ማግኘት ቀርቶ በአይኑ ለማየት አለመቻል፤ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማግኘት ያለመቻላቸውና የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየናረ መምጣት፤ አንድ አርሶ አደር ወደ ወረዳ ማዕከል ለመድረስ ከአንድ ቀን በላይ ለሚፈጅ ጊዜ በእግሩ መጓዝ የግድ እየሆነበት ስለመጣና ይህም ስላሰለቸው፤ ያላግባብ እንዲርቀው የተደረገው የወረዳ ማዕከል በሚፈልገውና ወደ ሚቀርበው ሥፍራ እንዲዛወርለት ያቀረበው ተደጋጋሚ አቤቱታ ሰሚ ሊያገኝ አለመቻሉ፤ ጥያቄውን ለመንግሥት በየደረጃው በተደጋጋሚ አቅርቦ መፍትሄ አለማግኘቱ ሕዝቡን በጣም አሳዝታል። በዚህም የተነሳ የዳውሮ ዋካን ሕዝብ ጥያቄ ያነገበው ጀግናው ሰማዕት መምህር የኔሰው ገብሬ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና የመልካም አስተዳደር እጦት በመቃወምና ድርጊቱን በማውገዝ ራሱን በእሳት በማቃጠል መስዋዕትነት መክፈሉ ይታወቃል። ይህም ሆኖ የዳውሮ ሕዝብ በደል መፍትሄ እስካሁን ሊያገግኝ አልቻለም።
የተቃውሞው እንደገና መቀስቀስ ምክንያት
ህወሐት/ ደኢህዴን በደቡብ ክልል በአንዳንድ ዞኖች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሳበትን የህዝብ ተቃውሞ መቀነስ ስለሚችልበት ሁኔታ ተወያይቶ ነበር። በዚህ ውይይት ላይ በዋናነት የተነሳውና የታመነበት ነጥብ የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄና የወረዳ ማዕከል ጉዳይ ሆኖ በውይይቱ ጎልቶ ወጣ። በመቀጠልም እንዴት አድርገው የህዝቡን ቁጣ ማርገብ እንደሚቻልና ምንም ተጨማሪ ወረዳ ሳይሰጥ ሕዝቡን የማሳመን ሥራ መሥራት እንደሚገባ ታምኖበት ለአፈጻጸም ለሚመለከተው የፖለቲካ ኃላፊዎች እንዲያስፈጽሙት ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ሕዝቡ እንዲወርዱ ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ በአንክሮ የተነሳው የቀድሞው ሰሜን ኦሞ ዞን ሥር የነበሩት ዞኖች መካከል የጋሞጎፋና የዳውሮ ዞኖች ህዝብ ጉዳይ ነበር። በዚህ መነሻነት የዞን አመራሮች ሕዝባቸውን የማሳመን ሥራ እንዲሰሩ የሚያስገድድ መመሪያ ለዞኑ የፖለቲካ አመራርች ይወርዳል። አመራሮቸ እንዲያስፈጽሙ ታዘዙ። በዚህ መነሻነት ነው እንግዲህ በእስርና በእንግልቱ ሳቢያ ዝም ያለና ጊዜ የሚጠብቅ፤ ግን ውስጥ ውስጡን እየፋመና እየጋመ የነበረን የህዝብ ብሶት እንደገና ቀሰቀሱት።
የዳውሮ ህዝብ ያቀረበው የፍትና የመብት ጥያቄ በመሆኑ ከዛሬ ነገ ይመለስልኛል ብሎ በሚጠበቅበት ወቅት መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጥያቄውን ለማድበስበስና ከሕዝቡ የተሻለ ለሕዝቡ አሳቢ በመምሰል ወረዳ ምን ያደርግላችኋል? ልማት ነው የሚያስፈልጋችሁ! ከልማትና ከወረዳ ምረጡ! ተጨማሪ ወረዳ አይጠቅማችሁም! የወረዳ ርእሰ ከተማ ቢርቅባችሁም ራቀብን አትበሉ! ዝም በሉ! እንዲያውም ፍትህ ፍለጋ ስንቅ ተሸክማችሁ በእግራችሁ ረጅም ሰዓት በመጓዛችሁደስ ደስ ሊላችሁ ይገባል! የሚል ስሜት ያዘላ አድራቂ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ለማወናበድ እየተሞከረ ይገኛል። የመንግሥት ሠራተኛው የህዝብ ልጅ እንዳልሆነና የሕዝብ በደልን የማይረዳ በማስመሰል ከሕዝቡ ሓሳብ በተቃራኒው ከአመራሮች ጎን እንዲቆም ለማድረግ በየወረዳው ካድሬ ተመድቦ ተግቶ እንዲሰራ ይደረጋል።
ካድሬዎች በሕዝቡ መካከል እጅግ የሚገርምና ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ጀመሩ። የማረቃ ዋካ ወረዳ ዋና ከተማ ዋካ ይሁንልን የሚልን የህዝብ ጥያቄ ለማፈን የማይቻል መሆኑ ግልጽ ነው። በማሰር በማፈን በሐሰት በመክሰስና በመወንጀል በማስፈራራት ጥያቄውን ምላሽ እንዳያገኝ ማድረግ አምና ተችሏል። ይህ ማለት ግን ሕዝቡ ጥያቄውን ትቶታል ወይም መልስ አግኝቷል ማለት አይደለም። የወረዳው ማዕከል አያማክለንም የሚለውን የሕዝብ ጥያቄ ለማፈንና ምላሽ ላለመስጠት ሲባል ለዘመናት አብሮ የኖረንና ቤተሰብ የሆነውን የማሪና አካባቢውን ሕዝብ በመቀስቀስና በዋካ ከተማ ሕዝብ ላይ ለማነሳሳት መቀስቀስ ቀጠሉ።
የማረቃ ወረዳ ሕዝብ ከቆዳ ስፋቱና ከሕዝብ ቁጥር አንጻር እንዲሁም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ የተነሳ ሁለት ወረዳ ሊሆን ይገባል የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት ያለው ነው። በዚህ የተነሳ ዋካና ማሪ ሁለት የተለያዩ ወረዳዎች መሆን ይገባቸዋል የሚል ሐሳብ ይዞ መነሳት ነው የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ ማለት። ነገር ግን ቀድሞ የነበረን ወረዳ የወረዳው ማዕከል ይርቀናል አያማክለንም የሚልን ጥያቄ ለማፈን ሌላ ተገቢ ያልሆነ ቅስቀሳ ሕዝብ ውስጥ መርጨት ተጀመረ።
በምንም ዓይነት ሁኔታየኢትዮጵያ ዋና ከተማ ኬንያ ጠረፍ የሚገኝ ቀበሌ ሊሆን አይችልም። የትግራይ ክልል ዋና ከተማ ደሴ አልተደረገም። ዳውሮ ውስጥ ብትመለከቱ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። የሎማዲሳ ወረዳ ዋና ከተማ ገሳ ጨሬ ይባላል። ይህ አዲስ የተቆረቆረ ከተማ ያለው በአጎራባቹ የጌና ቦሳ ወረዳ ውስጥ ነው። የሎማ ዲሳ ወረዳ ሕዝብ የጠየቀው የወረዳችን ዋና ከተማ ከአጎራባች ወረዳ ወጥቶ ቢያንስ እንደቀድሞው ወደ ወረዳችን መሐል አካባቢ ተመልሶ በሚያማክለን ሥፍራ ይደረግልን ነው። ይህንን ጥያቄ አይቶና ሰምቶ መፍትሔ የሚሰጥ አመራር የለም።
በመንግሥት ውሳኔ የተጣመሩ ወረዳዎች ዳግም በመንግሥት ውሳኔ ተለያይተው ቀድሞ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሲደረግ የወረዳው ማዕከል ጉዳይ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ውይይት ተደርጎበት ሊወሰን ሲገባ ይህ ሳይሆን ቀርቷል። ታዲያ ይሄ ስህተት የማነው? የሕዝቡ ነው ወይስ የአመራሩ ነው? ከዲሳ አካባቢ ለምሳሌ ቃኢ ጌሬራና ከዚያ ርቆ የሚኖር አንድ አርሶ አደር የወረዳውን አስተዳደር ፍለጋ አንድ ቀንና ከዚያ በላይ መጓዝ አለበት የሚል የወረዳና የዞን አመራር እውነት ለህዝቡ የቆመ ነው? አመራሩ ለምንድነው የሚመራውን ሕዝብ የማይሰማው? እውነት አሁን የዲሳ አካባቢ ህዝብ ወደ ገሳጨሬ እንዲመላለስ ተገቢ አይደለም ያለ የመንግሥት ሠራተኛ ሊዋከብ ሊታሰርና ከሥራ ሊታገድ ተገቢ ነው?
የዳውሮ ህዝብ የወረዳ ማዕከል ለአቤቱታ ሲሄድ እንደ ዘመነ ምንሊክ ከቤቱ ስንቅ ቋጥሮ በእግሩ ከአንድ ቀን በላይ በመጓዝ ላይ ይገኛል። በሎማ ወረዳ ዲሳ አካባቢ አገልግሎት ማለት ጋሞ ጎፋ ዞን አዋሳኝ አካባቢየሚገኝ ቀበሌ ማለት ነው። ከዚያ ተነስቶ አንድ አርሶ አደር የወረዳው ማዕከል ወደተሰደደበት ሌላ ወረዳ ማለትም ጌና ቦሳ ወረዳ ከአንድ ቀን በላይ መጓዝ ግድ ይለዋል። ከዚያ በኋላ ተጨማሪ የመኪና ጉዞ አድርጎ ነው ገሳ ጨሬ የሚደርሰው። ይህ ነው እንግዲህ እውነቱ። ልዩነቱ ጥቂት የእግር ጉዞ ሰዓታት ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ችግሩ በቶጫም ሆነ በማረቃ ወረዳዎች ተመሳሳይ ነው።
የሎማን ወረዳ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ የቶጫ ወረዳም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ተርጫ አጠገብ ዋራ አካባቢ የሚኖርን አንድ አርሶ አደር ከጪ ድረስ ተጉዞ ፍትህ እንዲያገኝ ማስገደድ ምን ይባላል? ከጪ ኢሰራ ወረዳ አጠገብ ነው። ቀደም ሲል ኢሰራና ቶጫ ወረዳዎች እንዲጣመሩ በተደረገ ጊዜ ሁለቱን ወረዳዎች እንዲያማክል በሚል የተመሰረተ ከተማ ነው። ወረዳዎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሲወሰን የኢሰራ ወረዳ ከተማ ወደ ቀድሞው ማዕከል ሲመለስ ቶጫ ወረዳ ግን ቀደም ሲል ወደ ነበረበት ሥፍራ ሳይመለስ እዚያው እንዲቀጥል ተደረገ።
ይህ የሕዝብ ጥያቄ ሕብረተሰቡን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ያስተባበረና እያጠናከረው የመጣ ሲሆን በገዢው ፓርቲ ላይ ያለው ጥላቻ እያደገና እየከረረ መጥቷል። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት ካድሬዎች ናቸው። ጀግናው የነጻነት ታጋይና ሰማዕት የሆነው መምህር የኔሰው ገብሬም “ የወረዳና የልማት ጥያቄ በማቅረቡ ወህኒ ቤት ሲያስሩት ጤነኛ የነበረ፤ ሲፈቱት ያልታመመና በሳምንቱ ራሱን በብሶት በቤንዚን አቃጠለ። በተቃጠለ በሦስተኛው ቀን ሞተና ከሞተ በኋላ ደግሞ ፖለቲከኞቹ እንዲሉት ታዘውና ተገደው እብድ ነበር አሉት። የከፈለው መስዋዕትነት የዚሁ ትግል አካል ነበር። ሌሎችም ለሚዲያ ያልበቁ በየወረዳው ፍትህና መልካም አስተዳደር እጦት ለችግራቸው መፍትሄ የሚሰጥ አካል አጥተው በተለያየ መንገድ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። ጊዜና ወቅት ሲፈቅድ የሚታወሱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
እኛ አመራሮቹ የምንፈልገውን አስተጋቡልንም? የወረዳ ጥያቄ ለህዝቡ አይጠቅምም እያላችሁ ሕዝቡን ቀስቅሱልን! የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን ከገዢው ፓርቲ ጋር ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ መተባበር ግዴታው ነው! ይህን ካላደረግህ ጥገኛ ነህ! በሌላ አባባል ህዝቡን ለማፈን መብቱን ለመንፈግ ተነስተናልና የመንግሥት ሠራተኛውም ከእኛ ይተባበር የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ወስነው ለመንግሥት ሰራተኛው ጥሪ አደረጉ። ለዚህ ያልተባበረውን የመንግሥት ሠራተኛ ከሥራ በማገድ በማባረር በማሰር ወዘተ ለማስገደድና አንገቱን ለማስቀርቀር ብሎም ዝም ለማሰኘት ይቻላል በሚል እርምጃ መውሰድ ጀመሩ።ይህም የሕዝቡን ቁጣ እየቀሰቀሰው ይታያል። ረዳት ሳጅን ሽታዬ ወርቁም ታህሳስ 17/ 2005 ዓ.ም በገሳ ጨሬ ከተማ የተደረገው የመንግሥት ሠራተኞች ስብሰባ ላይ አካሄዱን ያወገዘው። ሕዝቡን ማፈን ተገቢ አይደለም ያለው።
የረዳት ሳጅን ሽታዬ ወርቁ ጥያቄና ላቀረበው ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽም የዚሁ ውሳኔ አካል ነው። በደረሰበት ጫናና እስራት የተነሳ ነው ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ለመኖር መቸገሩን ያስታወቀው። ይህንን የሚያደርጉ ካድሬዎች ነገ ከሕዝቡ ጋር የሚኖሩ ናቸው ወይስ አይደሉም? እያልኩ ራሴን ስጠይቅ ምላሽ አጣለሁ። መንግሥትም የዳውሮ ሕዝብ ችግርን በመናቅ ጉዳዩ ለስልጣኑ ምንም የሚያሰጋው ስላልሆነ ይመስላል እስከዛሬ እያስለቀሰው ይገኛል።
ይህንን የዳውሮን ሕዝብ በደል ለማስቆም ትልቁ ጉልበት ያለው በመንግሥት እጅ መሆኑ ግልጽ ነው። መንግሥት ግን ስለ ሕዝቡ መበደል አልተገነዘበም ወይም ንቆታል አሊያም ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ዳውሮ ውስጥ ከፈጠራቸው አሽከሮቹ የሚቀርበውን የሐሰት መረጃ በመቀበል ሕዝቡን እንደጠላቱ ፈርጆታል ብዬ እገምታለሁ። በመሆኑም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚመለከታችሁ የሕብረተሰቡ አካላት የየድርሻቸውን መወጣት እንደ አለባቸው በማመን መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
መልዕክት ለሕወሀት አመራሮች
የዳውሮ ሕዝብ በደል እጅግ ተባብሷል። ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ያገኛል ብሎ ተስፋ ያደርግ ነበር። የሕዝቡ ጥያቄ በአጭሩ፤ የወረዳ ማዕከል ቦታ እንዲሆን የተመረጠው ሥፍራ የወረዳውን ሕዝብ አያማክልም፤ የወረዳ ዋና ከተማ ዝውውር የተወሰነውና የተከናወነው በአንድና ሁለት ካድሬዎች የግል ፍላጎትና መነሻነት ነው፤ ስለዚህ በሕዝቡ ፍላጎትና ሕዝቡን በሚያማክል ሥፍራ ይደረግልኝ ነው። ቅን መሪ ቢኖርና የመወሰን ኃላፊነት ከተመጣጣኝ ሥልጣን ጋር የተሰጠው ዜጋ ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንደማይቸገር ግልጽ ነው። ይህ ባለመሆኑ ሕዝቡ ተበደለ።
የሕወሀት/ ደህዴን ኃላፊና የአሁኑ “ ጠቅላይ ሚንስትር ” የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሰሩትና የሚያከናውኑት ድርጊት የዳውሮ ሕዝብ ጥላቻቸው እስካሁን እንዳልበረደላቸው ያሳያል። የዳውሮ ሕዝብ እምነት ያለውን ጠንካራ አመራር ጠራርገው አስወግደው፤ በቀጣይም ሌላ የተሻለ መሪ እንዳይፈጠር አምክነው በግል አሽከሮቻቸው ተክተውታል። እሳቸው በስልጣን እስካሉ ድረስ የዳውሮ ሕዝብ ለማንኛውም ፍትሐዊ ጥያቄው ምንም ምላሽ እንደማያገኝ እሳቸውም ያውቃሉ፤ አሽከሮሻሸውም ለዚሁ ሳይታክቱ ይሰራሉ፤ የዳውሮ ሕዝብም ይህንኑ በሚገባ ያውቃል። ይቃወሙናል በሚል የዳውሮ ከፍተኛ ባለሙያዎች በተለያየ ሰበብ ከሥራ ገበታቸው እየተወገዱ ይገኛሉ።
የእርሳቸው ዓላማ የዳውሮ ሕዝብን ጥቅም ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ነጥቀው የራሴ ነው ለሚሉት ብሔር አሳልፈው የመስጠትና የመጥቀም ራዕይ ነው። ለምሳሌ ያህል በዳውሮ ውስጥ የተካሄደውን የሰፈራ ፕሮግራም የሥራ ክንውን፤ በግልገል ግቤ ቁጥር ሦስት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ግንባታ ሥራ ከባለሙያና ከአስተዳደር ሠራተኞች ቅጥር ጀምሮ ከኃይል ማመንጫው ሥራ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ የተከላ ሥራ እንቅስቃሴዎች ድርጊቱን መመልከት በቂ ማስረጃ ነው። በወላይታ በኩል ብቻ ግንኙነት እንዲኖረው በማሰብ የዳውሮ ጠንባሮን የገጠር መንገድ ፕሮጀክት ሥራ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው አስዘግተውበታል። የዳውሮ ሕዝብ የወረዳ ጥያቄም እስከ አሁን መፍትሔ እንዳያገኝ ያደረጉ እሳቸው ለመሆናቸው የዳውሮ ሕዝብ ጥርጥር የለውም።አሽከሮቻቸውም ለሚቀርባቸው ሁሉ ይህችን ለሕዝቡ አረጋግጠዋል።አቶ ሺፈራው ሽጉጤ የደቡብ ክልል አስተዳዳሪ በዋናነት በዳውሮ የወረዳ ጥያቄ ጉዳይ አቶ ኃይለማርያም ያሳረፉትን በደል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለሕዝቡ ወረዳ በመስጠት ችግሩን ለመፍታት እንኳ እንዳይችሉ ተደርገዋል።
ህወሀቶች ከአቶ ኃይለማርያምና ከግል አሽከሮቻቸው ጡጫና በደል የዳውሮን ሕዝብ ታደጉ አላቅቁትም። ታግላችሁ የደማችሁት እናንተ ናችሁና እናንተው ብትበድሉት ይሻላል እሳቸው ከሚበድሉት። በደልን ማንም በደለ ያው ነው። ግን የእሳቸው በደል ባሰበትና ነው። እርሳቸው እንደሚሉት የዳውሮ ሕዝብ አሸባሪ፤ ጥገኛና ጸረ ልማት አይደለም። የሚጠቅመውንም የማያውቅ ሕዝብ አይደለም። የወረዳና የልማት ጥያቄን ልዩነትና አንድነት ጠንቅቆ ያውቃል። ለወላይታ ሕዝብ አምስት ተጨማሪ ወረዳ ሲሰጡት አቶ ኃይለማርያም የወላይታን ሕዝብ ጥገኛ ነው አላሉም። ጭቁን ሕዝብ ነው ብለው ነበር የሰጡት። ዛሬ የዳውሮ ሕዝብ የወረዳ ጥያቄ ከወላይታ ሕዝብ ቀድሞ ያቀረበ መሆኑን እያወቁ የተዛባ ሥም ሊሰጡት አይገባም። ይህንን ለምን ታደርጋለህ? የሚል ሰው የለም! እርሳቸውና የአሽከሮቻቸው የግፍ አገዛዝ ዘመን በዳውሮ ምድር ሊያበቃ ይገባልና የዳውሮን ሕዝብ ከእሳቸው ጡጫ አውጡት።
የወረዳ ጥያቄን ለማምከን ሲባል ወረዳውን በሁለትና በሦስት መንደር ከፋፍሎ የአንዱን መንደር ሕዝብ በሌላኛው ላይ ጥገኛ ሕዝብ ነው ታገሉት ብሎ መቀሰቀስ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ሕዝብ ሁልጊዜ አብሮ የሚኖር ነው። መንግሥት እንደነባራዊ ሁኔታው ሊቀያየር ግድ ነው። የሚቀየርና የሚያልፍ መንግሥትና ገዢ ፓርቲ ለዘመናት የኖረንና ወደፊትም አብሮ የሚቀጥል ሕዝብን ጥገኛ ነው፤ የጥገኛ ሐሳብ ተሸካሚ ነው፤ ጠላትህ ነው! ወዘተ በሚል ሕዝብን በጥላቻ እንዲተያይ ማድረግ አይጠቅምም። ይህንን ኃላፊነት ለጎደላቸው ከፍተኛ አመራሮች ንገሯቸው።
መልዕክት ለዳውሮ ዞንና ለየወረዳዎቹ ካድሬዎች
የዳውሮ ወረዳዎች የማዕከል ጥያቄ የተነሳው አሁን በእናንተ ዘመነ ሥልጣን አይደለም። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት አመራሮችም ሆኑ ካድሬዎች ለችግሩ መነሻዎች እንዳይደላችሁ እረዳለሁ። የችግሩ ምንጭ ቀደም ሲል የወረዳዎች መታጠፍና እንደገና መዘርጋት ጥሎ ያለፈው ችግር እንደሆነም አስተውላለሁ። ችግሩን ለመፍታት ከጪ፤ ገሳ ጨሬና ተርጫ ቤት የሠሩና የንግድም ሆነ ሌሎች የግል ድርጅቶችን የመሰረቱ ከፍተኛ ካድሬዎች የሚያሳርፉት ቀጥተኛ ያልሆነ ግፊትና ጫናም እንዳለ ይሰማኛል። በየወረዳው ማዕከል የተሰሩ የአመራሮችና የካድሬዎች የግል መኖሪያ ቤቶች፤ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለዚህ የወጣው ወጪ ወዘተ ቀላል እንዳይደለም አልዘነጋም። ይህ ሁሉ ግን ከምንመራው ህዝብ መብት የሚበልጥ አይደለም።ተጠቃሚው ሕዝብ አይመቸኝም ሲል ያለው አማራጭ መቀበልና በሕዝብ ውሳኔ መገዛት ይገባችኋል።
ይህንን የቤት ሥራና የዳውሮ የወረዳዎችን የማዕከል ጥያቄ በቀላሉ መመለስ ሲችል የሰሜን ኦሞ ዞን መዋቅር ፈርሶ በ1993 ዓ.ም መግቢያ አካባቢ ዳውሮ እንደ ዞን ሲዋቀር በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ አመራሮች ይህንን ችግር በሚገባ አስተውለው መወሰንና በቀላሉ ማስተካከል ሲገባቸው ይህንን ችግር ተክለው እንዳለፉ ይሰማኛል። ይህ የዛሬው የዳውሮ የአያማክለኝም ጥያቄና ችግር በሂደት ሊመጣ እንደሚችል አስቀድመው ማየት የቻሉ የዳውሮ ምሁራንና ባለሙያዎች ነበሩ። አስተያየታቸውን አቅርበው እንደነበር አውቃለሁ። ወረዳዎች እንዴት በአዲስ መልክ ቢካለሉ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል አጥንተው ያቀረቡት ነገር ነበር። ይህንን ጥናት አስፍቶ ሕዝብን ማወያየትና የተሻለ መፍትሄ ማምጣት አልተቻለም። የዚያኔ አስፈላጊ የነበረው ወረዳና የወረዳ ማዕከል ጉዳይ እንደተራ ነገር ታይቶ መፍትሄ ሳያገኝ ቀርቷል። ሕዝብ ተንቋል።
የቶጫ ወረዳ ሕዝብ የመኪና መንገድ በመቆፈር ግንኙነት መቁረጡን አትዘነጉትም። ይህን ያደረገ ህዝብ አቅም ቢኖረው ኖሮ ለደረሰበት በደል የተሻለ እርምጃ አመራሩ ላይ ይወስድ እንሰነበር ለመገመት የሥነ ልቡና ትምህርት አይጠይቅም። ተቃውሞውን አሳይቷል። በተመሳሳይ የዋካንና አካባቢውን ሕዝብ የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ባለፈው ዓመት አይታችሁታል። የዲሳን ሕዝብ ብሶት ደግሞ ሰሞኑን እያያችሁት ነው።
ጋሞ ጎፋና ዳውሮ የተለያዩ ናቸው። አቶ ታገሰ ጫፎ ወደ ደጋማው የጋሞ አካባቢ ተንቀስቅቅሶ የሕዝብ ፍላጎት የነበረውን የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ ለማምከን ባደረገው ጥረት ውጤታማ ሥራ ሰርቷል በሚል ተሞክሮ ይህ ሂደት በዳውሮ ሕዝብም ላይ ይሞከር በሚል የዳውሮ ሕዝብ እንደላቮራቶሪ እንዲሞከርበት አሥራ አንድ ገጽ ወረቀት ለውይይት የቀረበ ሰነድ በሚል ተዘጋጅቶ ተሰጥቷችሁ የሕዝቡን ጥያቄ ለማፈን እየሰራችሁ ትገኛላችሁ። ለዚሁም አፈጻጸም እንዲመች አስተያየት እንዲሰጥ የመናገር ዕድል ለማን እድል መስጠት እንዳለባችሁ ጭምር ተነግሯችሁ በነጻነት መናገር ለሚችሉ አርሶ አደሮች የመናገርና ሀሳባቸውን መግለጽ እንዳይችሉ በሕዝብ ስብሰባው ላይ እድል በመከልከል፤ እንቢ ብለው ከተናገሩ አቅራቢያችሁ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በማሰር ማፈን፤ የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ ደግሞ በተጨማሪ ማስፈራራት ከሥራ ማገድ እንዲሁም ከሥራ ማባረር ወዘተ ተግባራዊ በማድረግ የህዝብን ጥያቄ መቀልበስ እንደሚገባ ከሰነዱ ላይ ሰፍሯል። እየሰራችሁ ያላችሁትም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ነው። በዋናነት የጋሞጎፋ ሕዝብ ጥያቄ የተጨማሪ ወረዳ ጭምር እንጂ በጉልህ የወረዳ ማዕከል ጥያቄ አልነበረም።
ባለሙያዎች የሆናችሁ አመራሮችና ካድሬዎች በሙያችሁ ሰርታችሁ በቀላሉ መኖር የምትችሉት ዜጎች ናችሁ። እውነትን ሰርቶ ማለፍ የህሊና ቁስል የለውም። እስቲ የሚከተሉትን ጥያዌዎች ልጠይቃችሁ። ሲዳማ ዘጠኝ፤ ወላይታ አምስት፤ ቤንች ማጂ ሦስት፤ ስልጢ ሁለት፤ ጎፋም እንደዚሁ አዳዲስ ወረዳዎች ለሕዝቡ ሲሰጥ ለምን የነዚህ ዞንና ወረዳዎች አመራሮች ህዝቡን ወረዳ አያስፈልገውም ልማት ይጠቅመዋል ብለው ወረዳውን ያላስከለከሉትና ሕዝባቸውን ያልቀሰቀሱት ለምንድነው? ምናልባት አመራሩ ጥገኛ ስለሆነ ነው ትሉኝ ይሆናል። ለሲዳማ አቶ ሺፈራው፤ ለወላይታ አቶ ኃይለማርያም፤ ለስልጢ አቶ ሬድዋን፤ ለቤንች ማጂ አቶ ጸጋዬ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት ለሕዝባቸው አዳዲስ ወረዳዎችን ሰጧቸው። እርግጠኛ ነኝ እነዚህን አመራሮች ጥገኛ ናቸው እንደማትሉ! ታዲያ ዳውሮ ውስጥ ተጨማሪ ወረዳ መጠየቅ ይቅርና የወረዳ ማዕከል ይስተካከልልኝ ብሎ ማሰብ መናገርና መጠየቅ ምነው ጥገኝነት በሚል ፍረጃ ውስጥ የሚያስገባ ሆነ? የዳውሮ የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ለምን ከልማት ጋር ይያያዛል? እናንተ ለህዝባቸው ወረዳ ከሰጡት ባለስልጣናት የምታንሱት ሕዝባችሁን ስለማትወዱና ራሳችሁንና የሥልጣን ዘመናችሁን ለማስረዘም ብላችሁ ነው የሚል ጥያቄ ቢነሳባችሁ መልሳችሁ ምን ይሆን? ቀድሞውኑ ማን ጠይቋችሁ!
በቀድሞዎቹ የንጉሡና የደርግ መንግሥታት ዘመን ያገለገሉትና ሕዝብን በድለዋል ተብለው ብዙ ባለስልጣናት ታስረዋል ተቀጥተዋል። እነዚህ ባለሥልጣናት አብዛኛዎቹ ያገለገሉበት መንንግሥት የሰጣቸውን ሥራ በሕዝቡ ላይ አስገድደው አስፈጽመዋል። ትልቁ በደላቸውና ስህተታቸው ይህ እንደሆነ ሲገለጽ ሰምተናል። የመንግስትን ዕቅድና ፍላጎት በጉልበት ማስፈጸም፤ የግለሰብን የመናገርና የማሰብ ነጻነት መንፈግ፤ ያለምንም ጥፋትና በደል ሰውን በመናገሩ ብቻ እንደወንጀለኛ ማሰር ማንገላታት ከሥራ ማባረር ወዘተ ማድረግ ከቻላችሁ ታዲያ እናንተ ከእነርሱ የምትለዩት በምንድነው? እናንተስ ነገ ተመሳሳይ ጥያቄ እንደማትጠይቁ እርግጠኞች ናችሁ?
አትቀበሉኝ ይሆናል ግን ልምከራችሁ።‘‘ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል፡፡’’ ምሳሌ 29፡2 እናንተንን ክፉዎች ናችሁ ለማለት ባልደፍርም የዳውሮ ሕዝብ እያለቀሰ ነው። እውነቱን ደግሞ ውስጣችሁ ያውቀዋል። እናንተም ነገ ታልፋላችሁ። ለሚያልፍ ሥልጣን ብላችሁ የማያልፈውን ወገናችሁን በዋናነት ዳውሮንና ሕዝባችሁን አትበድሉ። የመሰለውን ስለተናገረ ሰውን አላግባብ ጎትታችሁ አትሰሩ። የደርግ ባለሥልጣናት እንኳን እንደናንተ ለሕዝብ እንዲዋሽ ትብብር ጠይቀው እንቢ አልተባበርም ያላቸውን ግለሰብ ስለማሰራቸው እርግጠና አይደለሁም። የእናንተ ባስ እኮ!
የመንግሥት ሠራተኛ የግል ሠራተኛችሁ አይደለም። እንደእናንተ ሕዝብን አልዋሽም ስላለ ከሥራም አንዲባረር እንዲጎሳቆል አታድርጉ። ቢቻላችሁ የህዝቡን ጥያቄ በምትችሉት ሁሉ መልሳችሁ ምኑም ቀርቶባችሁ በሰላምና በፍቅር ከወገኖቻችሁ ጋር ብትኖሩ ይሻላችኋል። ነገ ከስልጣን ስትወርዱ የምትኖሩት ከዳውሮ ሕዝብ ጋር ነው። ብትሞቱ የሚቀብራችሁ ይህ ህዝብ ነው። ቃሉን አክብራችሁ ብትሰሩ ይጠቅማችኋል። ወደዳችሁም ጠላችሁ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ አይቀርም። አሁን በሥልጣን ያላችሁት ግለሰቦች የሕዝቡን ጥያቄ በተገቢው መልሳችሁ ምርቃቱ ቢቀርባችሁ እንኳ ሳትረገሙ ብታልፉ ይሻላችኋል። ነገ ከነገወዲያ እግዚአብሄር ሲፈቅድለት በእናንተ ማግስትም ቢሆን የህዝብ ጥያቄ በተገቢነት መመለሱ እንደማይቀር ለማየት ዕድሜ ያድላችሁ!
ለመንግሥት ሠራተኞች
ረዳት ሣጅን ሽታዬ ወርቁ በሎማ ዲሣ ወረዳ አካባቢ የዲሣ ከተማ ፖሊስ በመሆን ለዓመታት ማገልገሉንና በቅርቡ ወደ ሎማ ገሣ መዛወሩን፤ በዲሣ አካባቢ ቆይታዉ ወቅት የዲሣን ወረዳ ጥያቄ የሚያንቀሳቅሱ ሦስት ግለሰቦችን እንዲያስር ከዳዉሮ ዞን የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ መመሪያ ተሰጥቶት ያለ አንዳች በቂ ማስረጃና ጥፋት ሰዉ እንዲሁ ከሜዳ አላስርም በማለቱ በዞኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሁኔታው አልተደሰቱም ነበር፡፡ የዲሣን ወረዳ ጥያቄ ያንቀሳቅሳሉና መታሰር አለባቸዉ ተብለዉ ከዞኑ ፖለቲካ ኃላፊ ትዕዛዝ የተላለፈባቸዉ ግለሰቦች አቶ አባቴ አሰፋ የትምህርት ባለሙያ፤ አቶ መስፍን ማሞ አርሶ አደር፤ እና አቶ ደስታ ቶልባ የግብርና ባለሙያ ነበሩ። አሁን እዚህ ላይ የፖለቲካ ኃላፊውንና ፖሊሱን አወዳድሩ። የትኛው ነው ለሕዝብ የቆመውና እውነተኛ የህዝብ ጥቅምና መብት የታገለው? ልዩነቱን ተመልከቱ።
ይህንን ያነሳሁት በየወረዳው እየተደረገ ያለው የሕዝብን እውነተኛ የተጨማሪና የወረዳ ማዕከል ይስተካከልልኝ ጥያቄ የመንግሥት ሰራተኛው እንዳይደግፈው ለማድረግ እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ ለማመላከት ነው። የመንግሥት ሠራተኛው የራሱም ሆነ የቤተሰቡ ህይወት መንግሥት በሚከፍለው የወር ደመወዙ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ካድሬዎች ይህችን እንጀራውን እንደማስያዣ ዕቃ ቆጥረው አንድን የመንግሥት ሠራተኛ እነርሱ የፈለጉትን እንደ ቴፕሪከርደር ሲዲ ያሻቸውን ሞልተው ለማናገር የወሰኑ ይመስላል።ልጅን በአባቱና በቤተሰቡ ላይ ለመቀስቀስ እየሰሩ ነው።
ኃላፊነት የጎደለው ሥራ እያተሰራ ይስተዋላል። የህዝብን ጥያቄ ለማፈን ለመንግሥት ከባድ አይደለም። እንደተለመደው ማሰር ማንገላታት ማስፈራራትና ጥያቄህን አንመልስም እንቢ ምን ታመጣለህ? በሚል በተለመደው መንገድ ማስቆምና መግታት ይቻላል። ተችሏልም። ነገር ግን አንድ ወረዳ ውስጥ ያለን የኖረንና የሚኖርን ሕዝብ እርስ በራሱ ለማጋጨት በአንድ ወረዳ ውስጥ የዋካንና ዙሪያውን ህዝብ ጥያቄ የማሪ ዙሪያ ህዝብ እንዲቃወመው ሕዝብን ማነሳሳትና መቀስቀስ፤ የዲሳን አካባቢ ሕዝብን የወረዳ ማዕከል ጥያቄን ለመቀልበስ የገሳጨሬ አካባቢ ሕዝብን መቀስቀስ፤ የቶጫ አካባቢን ሕዝብ ጥያቄ ለማፈን የከጪ አካባቢ ሕዝብን መቀስቀስ የዛሬን የሕዝብን የወረዳ ጥያቄ ለመግታት እየተሰራ ያለው ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ለነገ አብሮነታቸው የሚያሳድረው የነገር ቁርሾ እንዳይኖር በተማሩትና አርቀው ማስተዋል የሚችሉት የሕብረተሰቡ ወገኖች ሊያስቡበትና ሊነቁበት ይገባል። ካድሬዎቻችን ምን እንደነካቸው አላውቅም። እኛ በስልጣን ላይ ዛሬን እንቆይ እንጂ የሕዝብ ጉዳይ የነገ ጉዳይ ወዘተ አያገባንም ያሉ ይመስላልና እንድናስብ አደራ እላለሁ። እነርሱ ለሕዝባቸውና ለዳውሮ ጥሩና የሚችሉትን አድርገው ለማለፍ የታደሉ አይደሉም።
በ1998 ዓ.ም እና በ1999 ዓ.ም የሌሎች አካባቢዎች የዞንና የክልል አመራሮች የነበሩ ለህዝባቸው ልማትና ዕድገት ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም የማያስቀድሙ፤ ህዝባቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ፤ በተሰጣቸው የስልጣን ክልል የህዝባቸውን የልማትና የወረዳ ጥያቄ አንግበው የታገሉና ጸንተው የቆሙ፤ የወከለኝ ህዝብ ጥያቄ የእኔም ጥያቄ ነው ያሉ አመራሮች በሌሎች ዞኖችና አካባቢዎች በተለያየ ቦታና ደረጃ አሉ። የሲዳማን የስልጢን የጎፋን የቤንችንና የወላይታ አመራሮችን የሥራ ተግባር ማየት እንችላለን። እነዚህ ህዝባቸውን ጠቅመዋል። የወከላቸውን ሕዝብ ጥያቄ በሆዳቸው አልለወጡትም። በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የሞራል የበላይነት ሊሰማቸው ይገባቸዋል። ሕዝባቸውና አካባቢያቸው ሲዘክራቸው ይኖራል።
ለጊዚያዊ የግል ጥቅማቸው የቆሙ፤ ነገ ሳያውቁትና ሳይመሰገኑበት አሊያም ታስረው ወይም ተባርረው ለሚጥሉት ሥልጣን ትኩረት የሰጡ፤ ለጊዜው የያዙትን ሥልጣን ማጣት የሚያስጨንቃቸው፤ ራስ ወዳዶች፤ ጥሩ ነገር ለህዝባቸው ሰርተው ለማለፍ ያልታደሉና አድርጉ የተባሉትን ለማድረግ ተሽቀዳድመው ከመሮጥ ባሻገር ቆም ብለው ይህ ሕዝባችንን አካባቢያችንን ይጠቅማል ወስ አይጠቅምም? ሕዝቡስ ምን ይላል ማለት የማይችሉ የህዝብ ተቃራኒዎች ደግሞ አሉ።። የዳውሮ ዞን አመራሮችን በዚህ ቡድን አስገብቶ መውቀስ ተገቢ ነው። ጠንካራ አመራሮች ለህዝባቸውና ለዞናቸው ተጨማሪ ወረዳ ታግለው አስገኙ። እኛ ለህዝብ የቆመ አመራር በዞን ደረጃ ስላልነበረን የዳውሮ ህዝብ እያነባ እያለቀሰ ይገኛል። ከእሱ የተሰበሰበው ግብርና ታክስ እየተከፈለው የሚሰራ አመራርና ካድሬ ህዝቡ ወረዳ አያስፈልገውም አልጠየቀም እያለ እየዋሸ እኛም የሱን ግጥምና ዜማ ተቀብለን እንድናዜም ሊያስገድደን ይታገለናል። አለመታደል እኮ ነው ወገኖቼ! በፍጹም እንቢ ልንል ግድ ይለናል። ተቃውሟችሁን በግልጽ አድርጋችሁ ጥቂቶችን ሰለባ ማድረግ ባያስፈልገንም የሕዝብ አጋርነታችንን በምንችለው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተቃራኒ መግለጽ የሞራል ግዴታችን ነው።ይህ አመራር ጥቅሜ ከሚጓደልና የመኪና ጋቢና ከሚቀርብኝ ከዳውሮ ሕዝብ ምኑም ይቅርበት ብሎ የወሰነ ይመስላልና ያቅማችንን የማበርከት ግዴታ ይጠብቀናል።
ለዳውሮ አርሶአደሮች፤ ነጋዴዎችና ሌሎች የየከተማው ነዋሪዎች
ለዳውሮ ዞን ሕዝብ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጣችሁ በተስፋ ስትጠብቁ ቆይታችኋል። ነገሩ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚታወቅ ቢሆንም የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የሚል የፖለቲካ አመራር በየደረጃው ባለማኖሩ እስካሁን ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አልተቻለም። እንዲያውም እያደር ጥያቄው የጥገኞች ነው፤ የጥቂቶች ነው፤ የብዙኋኑ የዳውሮ ሕዝብ ጥያቄ አይደለም፤ ሕዝቡ ልማት እንጂ ወረዳ አይጠቅመውም በሚል የሕዝቡን ጥያቄ ለመቀልበስና አቅጣጫውን ለማስቀየር ብሎም ህዝቡ ተጨማሪ ወረዳ እንዲያጣና የሚሻውን የወረዳ ማዕከል ወደሚቀርበው ሥፍራ የማዛወር መብት እንዳይኖረው ለማድረግ ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ።
የገዛ ልጆችህ ናቸው ጥያቄህን ለመድፈቅ አሲረው አንተን ለማፈን ተግተው እየሰሩ የሚገኙት። የሚናገረውን ለማስፈራራትና እንዳይናገር በማድረግ እድል በመከልከልና በማሸማቀቅ፤ ለምን መብታችንን ትነኩብናላችሁ ብለው የሚጠይቁ ከተገኙ ለማስፈራሪያነት በማሰር ለማስፈራራት ዕቅድ ተሰጥቷቸው ይህንን ለመተግበር ይሰራሉ። በመንደርና በአገልግሎት በመከፋፈል ጥያቄህን ለማሳነስና የጋራ ጥያቄ አይደለም የጥቂቶች ነው ለማለት እየተባበሩ ነው። ስለዚህ በአገልግሎትና በመንደር መከፋፈል አያስፈልግህም። ልማትና ወረዳ አይነጣጠልም።
አንድ ምሳሌ ላንሳላችሁ። የወረዳ ማዕከል ጥያቄ የእኛ አይደለም የጥቂቶች ነው እኛ ወረዳ አንፈልግም በሉ፤ እንቢ ካላችሁ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱን ከዚህ እናነሳለን፤ የጤና ጣቢያ ሥራ አይከናወንም ወዘተ የሚል ተራ ማስፈራሪያ አንድ ሆድ አደር ካድሬ ሲናገር ሰምተው ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንዱ አርሶ አደር (በማረቃ ወረዳ ጌንዶ አገልግሎት አካባቢ ውስጥ ነዋሪ ናቸው ) ካድሬውን በሚያሳዝን መልኩ ረግመውት አሁን የእኛን ወረዳ ጥያቄ ለማስጨንገፍ ብለህ ለሆድህ አድረህ ህሊናህን ሽጠህ በል የተባልከውን እያልክ ነው ብለዉት ይህንን ተራ ወሬ ይዞ ወደ መጣበት እንዲመለስና እሳቸውም ሆነ ሕዝቡ የሚሻለውን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆኑን አስተምረውት አሳፍረውት መልሰውታል።
ይህንን የተናገሩት አርሶ አደር በፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና አንጻር ከካድሬው ጋር አነጻጽራችሁ የቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳለ አስተውሉ። ማነው የህሊና ነጻነት ያለው? ልማትና ወረዳ አይነጣጠሉም። ወረዳ ሲመጣ ከወረዳው ጋር አብሮ ልማትም ይመጣል። ዳውሮ ዞን ባይሆን አሁን የደረሰበት የልማት ደረጃ ላይ ይደርስ ነበር የሚል ካድሬ ሊመጣ እንደሚችል አትጠራጠሩ ግን አትመኑት። የሰሞኑ ካድሬ ድንጋይ ዳቦ ነው ለማለት የሚታቀብ ስለመሆኑ ያጠራጥራል። እያከናወነ ያለው ክብሩን ህሊናውን ሞራሉን ሁሉ ትቶት ነው።
የዳውሮ ሕዝብን የወረዳና የልማት ጥያቄውን ለመቀልበስ የሚሰሩ ሁሉ የዳውሮ ልማትና የዳውሮ ህዝብ ጠላቶች ናቸው! ሕዝብ የሚበጀውንና የሚሻለውን ያውቃል። የካድሬ ሰበካና የሐሰት ቀላጤ አያስፈልገውም። የካድሬው ዓላማ የህዝብን ጥያቄ ወደ ጥቂቶች ጥያቄነት ለመቀየርና ጥያቄውን ለማምከን ነውና ሁላችንም በምንም ሳንከፋፈል አብረን ቆመን ጥያቄያችንን በጋራ በአንድ ድምፅ ማስተጋባት ይጠበቅብናል።
የዳውሮ ምሁራን የሆናችሁ በሙሉ!
ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥኩትን እውነታ ተመልክታችኋል። የዳውሮ ዞን አመራሮች ከክልል አመራሮች ተጭነው የመጡትን የሕዝቡን የወረዳና የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ለማምከን ምን ያህል ተግተው እየሰሩ እንዳለ ተመልከቱ። ከራሳቸው አልፈው የወረዳ አመራሮችንና ካድሬዎችን አስገድደው የተጫኑትን መልሰው ጭነውባቸው ከህዝቡ ጋር እያላተሟቸው ይገኛል። እኔ በግሌ የወረዳ አመራሮች ላይ ብዙ አልፈርድም። ለአብዛኛዎቹ የእንጀራ ጉዳይም ሆኖባቸው ሳይወዱ በግድ የተጫኑትን ማራገፊያ አጥተው እንደሚሰቃዩ ይሰማኛል። ከሕዝቡም እየደረሰባቸው ያለው ነገር እያሰቃያቸው ነው። በድርጊቱ ከዞን ጀምሮ ያለው አመራር በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም በደልና እንግልት ተጠያቂ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል።
ምሁሩ የሕዝብ ወገን አመራሩ ለምንድነው እንዲህ የሚያደርጉት? ምን ይሻሻል? ከእኔ ምን ይጠበቃል? በሚል ማሰብ እንደሚገባችሁና እንቅስቃሴውንም በአንክሮ መከታተል እንደሚጠበቅባችሁ አሳስቤ ጽሁፌን በዚሁ እቋጫለሁ።
No comments:
Post a Comment