የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በሃይማኖቶች የውሰጥ አስተዳደር የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት አሁንም በፊት ከነበረው በበለጠ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። የውስጥ አሰተዳደራችን ይከበርልን ብለው በሰላማዊ መንገድ በጠየቁ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ዘግናኝና አሳፋሪ ከመሆን አልፎ ፍጹም ኢ-ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ያሳሰበው ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) ከዚህ በፊት ድርጊቱን በማውገዝ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫው አቋሙን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ አድርጓል። በትዕቢት የተወጠረው ህወሓት/ኢህአዴግ ግን አሁንም በማናለብኝነት የእስልምና እምነት ተከታይ ማኅብረሰብ ተወካዮችን በአሸባሪነት አስሮ እያንገላታቸው፤ እያሰቃያቸውና እየገደላቸው መሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም። ይህ አጉራ ዘለል የመብት ረገጣ በተቃዋሚው ጎራ ብቻ ሳይሆን በውጭ መንግሥታትም ጭምር ተቃውሞ እየቀረበበት ያለ ቢሆንም ህወሓት/እህአዴግ ግን ከዚህ እኩይ ተግባሩ ሊታቀብ አልቻለም።
ህወሓት/እህአዴግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ሕግና ደንብ ውጭ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ወብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስን በመሣሪያ አስገድዶ ከመንበራቸው አውርዶ በማባረር የራሱ አባልና ደጋፊ የሆኑትን ሟቹን አቡነ ጳውሎስን መሾሙ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ጎራ ተከፍላ ስትታመስ ከርማለች፤ አሁንም ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ አልተላቀቀችም።
ህወሓት/ኢህአዴግ እራሱ ያወጣው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 27 “ማንኛውም ሰው በግልም ሆነ በስብስብ የፈለገውን ዕምነት የመከተልና ዕምነቱን የማዳበር፤ የማስተማር ሙሉ መብት አለው፤ መንግሥትም ጣልቃ አይገባም” ይላል። ይሁን እንጂ ህወሓት/ኢህአዴግ ይህን ሕገ-መንግሥት ተብዬው ለዜጎች የሰጠውን መብት እንኳን እየጣሰ በሃይማኖት ተቋሞች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነቱን ቀጥሎበታል። ይህ ሁኔታ እጅግ ያሳሰባቸው በሁለቱም በኩል ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሰላም እንዲወርድና ወብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ የውጣ ውረድ ውይይት በማካሄድ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ በለመዱት አምባገነናዊ አሠራር እነ አቶ አባይ ፀሐዬና አቶ ስብሃት ነጋ ጣልቃ በመግባት ሌላ ፓትርያርክ ለማስመረጥ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም ባስተላለፉት ቀጭን ትዕዛዝ መሠረት አገር ቤት ውስጥ አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቋሟል። ከአዲስ አባባ በኩል ለእርቁ መጥተው ከነበሩት አባቶች ውስጥ አንዱ እርቁ ሳይቋጭ ለምን ምርጫ እናደርጋለን ብለው ተቃውሞ በማሰማታቸው ከአገር እንዲባረሩ ተደርጓል። ይህንንም ጅብደኛው በረከት ስሞን ያለምንም ሃፍረት አባረነዋል ሲል ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል። በሃይማኖት ተቋም ውስጥ በገሃድ ጣልቃ ገብነት ይሏል ይሄ ነው!
የኢትዮጵያው ፕሬዘዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ወብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ የሚገልጽ ደብደቤ ጽፈው እንደነበረም ይታወሳል። ይሁን እንጂ ደብዳቤው የተፈረመበት ቀለም እንኳን ሳይደርቅ የተሰረዘ መሆኑን ሰምተናል። ይህ ሊሆን የቻለው በሌላ ምክንያት ሳይሆን አሁንም የነስብሃት ነጋ ጣልቃ ገብነት ለመሆኑ ማስረጃ የሚያስፈልገው አይደለም። አቶ ስብሃት ነጋ አሁን በቅርብ ቀን በመገናኛ ብዙሃን “ህወሓት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንንና የአማራውን የጀርባ አጥንት ስብሮታል” ብሎ ያለ ሃፍረት መናገሩ ምን ያህል በማናለብኝነት ትዕቢት መወጠሩን የሚያመለክት ነው።
ፀረ-ሰላምና ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነው የነስብሃት ነጋ ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ አፀደቅሁት ያለውን ሕገ-መንግሥት ለነሱ በሚያመች መንገድ እየተረጎሙ ሕዝብንና ሀገርን በሚያጠፋ ሜዳ እየጋለቡ ቁልቁለቱንም እየተንደረደሩ ነው። ይህ የመብት ረገጣና አፈና ሊወገድ የሚችለው የተቃዋሚው ኃይል ጠንካራ ኅብረት ፈጥሮ የተረገጠውንና የተበደለውን ሕዝብ አስተባብሮ በመምራት ሲታገል ብቻ ነው። በተነናጠል የሚደረግ ትግል ከኅብረት ትግል የሚገኘውን የፈረጠመ የትግል ውጤት ከመንፈጉም ሌላ ህወሓት/ኢህአዴግ በማናለብኝነት በሕዝባችን ላይ ለሚያደርገው መረን የለቀቀ የአፈና አገዛዝ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑ በፍጹም አጠያያቂ ሊሆን አይገባም።
ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) ህወሓት/ኢህአዴግ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎች ሁሉ አምርሮ ይቃወማል። በኢትዮጵያዊነታቸው ፀንተው በመቆማቸውና በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን የግፍና የአፈና አገዛዝ በማጋለጥና በመቃወም የሕዝብ ድምፅ በመሆናቸው ብቻ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው በእንበለ ፍርድ (ፍርድ አልባነት) የታሰሩት ንፁህ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ ይላል ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ)።
ሰፊው ሕዝብ ምን ጊዜም አቸናፊ ነው!
No comments:
Post a Comment