ከይኸነው አንተሁነኝ
ር 8 2013
ዘመናት ይቀያየራሉ፣ ወቅቶች ይለዋወጣሉ፣ የመሸው ይነጋል የጨለመው ይበራል፣ ገናና የነበሩት ነገስታት ዛሬ የሉም የሚተማመኑበት ሃይል ጭምር ተንኮታኩቷል፣ የነበሩት እያረጁ
አዲሶቹ እየተወለዱ ብርቱዎች እየደከሙ ደካማ የሚባሉትም እየጠነከሩ ቀጥለዋል። ሁሌም የለውጥ ንፋስ ባካባቢያችን ይነፍሳል። ከለውጡ ጋር ያሉ ይዘምራሉ ነፋሱ የሚገፋቸውም ያማርራሉ። ይህ የነበረ ያለና የሚኖር እውነት ነው። በፍቅር ስም የሚያጠፉ እንዳሉ ሁሉ ስለ ፍቅር ለሌሎች እራሳቸውን ቤዛ የሚያደርጉ ሽዎች ናቸው። ስለ ሀገር እያሉ ድንበርን የሚያያስደፍሩ ሀገርን የሚቆርሱና ተስማምተው የሚያስቆርሱ የመኖራቸውን ያህል የወገን ቁስል አሟቸው መሰደብ መገፋት ሰልችቷቸው መናቅ መዋረድ ገልምቷቸው መጎሳቆል መሳደድና ኢፍታዊነት አማሯቸው ስለ ወገን ክብር ለሕዝብ ልዕልና በሀገራችን ጋራዎች በርሃዎች ወንዝና ሸለቆዎች ውድ ሂዎታቸውን ያለስስት ሊሰጡ የወጡና እየወጡ ያሉ ዛሬም ብዙዎች ናቸው። ዛሬም ስለ ባንዲራችን ክብር ስለ ሀገራችን ታሪክና አንድነት መጠበቅ በዳር ድንበራችን ፈፋዎችና ጫካዎች እንዲሁም ወገን ባለበት ሁሉ የዘመራል። አዎ ለመዋደድ የተናገሩት ክቡር ቃል መሳለቂያ የሆነባቸው፤ ለፍቅር የዘረጉት እጅ ልብ በሚያደማ ድርጊት የተመለሰላቸው እህቶቻችን፤ መጨቆን መበደል መታረዝ መገደል በቃን፣ መናቅ መዋረድ ከሰው በታች ሆኖ መቆጠር አቃረን ያሉ ወንድሞች ዛሬም አዲስ ዓላማ ዛሬም አዲስ ወኔ ሰንቀው ወያኔን እራሱ በመረጠው ቋንቋ ለማናገር ጎህ ፈንጣቂ ተስፋ ሰጭ ጉዞ ጀምረዋል። ነገም አዲስ ቀን ነው ባዲስ ተስፋ የተሞላ- ግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል። የኔም የዛሬው መጣጥፍ ወያኔ በዚህ አዲስ እንቅስቃሴ ዙሪያ ምን ሲል እንደከረመ የሚዳስስ ይሆናል። አብራችሁኝ ቆዩ።
መቼም ሁላችንም እንደምናውቀው ወያኔዎች እየፈላ ባለ ውሃ ላይ የቡና ዱቄት ሲጨመር እንደሚፈጠረው ኩነት አይነት ናቸው። ድንገት ይገነፍላሉ። በማያስደነግጠው ሲደነብሩ፣ የሌለ ነገር ሲያዩና ሲየዳምጡ ኖረዋል። እራሳቸው ፈርተው ሕዝባችንን ሲያሸብሩት መቆየታቸውን መተረክ ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆን ለጊዜው ትቸዋለሁ። ለዛሬ ግን ፌስ ቡክን በመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛዎች በወያኔዎችና በወያኔ ጭፍን ደጋፊዎች የግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይልን በተመለከተ የተባለውን ለአሁን እንዝለልና የወያኔ ላንቃ ማላቀቂያ የሆነው ትግራይ ኦን ላይን ምን እንዳለ እንመልከት።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል ለሁላችንም አዲስ ክስተት ነው። እርግጥ ነው፤ አዲስ ነገር አዲስ ከመሆኑ አንጻር ያስደነግጣል የሚሉ ወገኖች አይታጡም። ሆኖም ግን ሁላችንም እንደምንረዳው የወያኔዎች የልብ ምት ሩጫ ጨምሮ እንደታየበት እንደሰሞኑ የትግራይ ኦን ላይን ዘገባ ግን አያደርግም። በሀገራችን እውነተኛ ዲሞክራሲን ለማየት እንሻለን፣ ፍትህ የሰፈነባት አኩልነት የነገሰባት ፍቅር ያበበባት አንድነት የጎመራባት ኢትዮጵያን ለማየት እንፈልጋለን ማለት ያስደነግጣል እንዴ? በነፃነት እጦት የሚሰቃዩ በፍትህ መጓደል የሚማረሩ እኩል እድል ለትምህርትና ለስራ ከማጣትም አልፈው በነፃነት የመኖር ተፈጥሮአዊ መብታቸውን አጥተው በግፍ ያለፍርድ ወይም በተዘናበለ ፍርድ ሂዎታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ጉዳይ አንገበገበን ማለት ያስደነብራል? ወይስ እኛ ትግሬዎች በጥርስ በጥፍራችን እስከ መጨረሻው አንድ ሰውና እስከ መጨረሻዋ የደማችን ጠብታ ድረስ እንዋጋዋለን በማለት የትግራይን ሕዝብ ወክሎ ትግራይ ኦን ላይን ያሰፈረው፤ የትግራይ ሕዝብ በወያኔ ስርአት በነፃነት እየኖረ ነው ብሎ አምኖ ከሆነ ስለ ትግራይ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት በትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስር ተሰልፈው ከወያኔ ጋር በመፋለም ክቡር ሂዎታቸውን መስዋት እያደረጉ ያሉትን የትግራይ ወጣቶች ላፍታ ማስታወስ የሚገባው ይመስለኛል። ካወጣው የመጀመሪያ መግለጫና ከራሱ ድረ ገጽ እንደምንረዳውም የግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል ለፍትህ ለነፃነት ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ የሚታገል ሃይል ነው። ወያኔዎች በትግራይ ኦን ላይን ላይ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንን ለማሳረድ የተፈጠረ ሃይል ነው ቢሉም ለፕሮፓጋንዳ ይውል እንደሁ እንጅ ያለ ደም መፋሰስ በሰላማዊ ትግል የታጡትን እነዚህን ውድ እሴቶች ለማግኘት የሂዎት መስዋትነት መከፈሉ አይቀሬ መሆኑን አጥተውት አይመስለኝም።
“የወሎ ደብተራ ቅኔ ቢጎድልበት ፉከራ ሞላበት” እንደሚባለው ወያኔዎች እንደተለመደው ማጣፊያው ሲያጥርባቸው እንደሚያደርጉት ሁሉ እነሱ የፈበረኩት መከራና ስቃይ የፈጠረውን ይህን የትጥቅ ሃይል (ግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይልን) ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሻቢያ እየረዳው ነው፣ በአባይ ወንዝ የይገባኛል ጥያቄ ያልተደሰተችው ግብጽ ያሰለፈችብን ሃይል ነውና ሌሎችንም በመደርደር ክቡር ዓላማቸውን ጥላሸት ለመቀባት እየቀባጠረ ይገኛል። ከዚህም እጅግ በተመጻደቀ መልኩ በ 7 ጠበንጃ የትጥቅ ትግል ጀምረን በወታደራዊ አቅሙ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትን ሃይል ጥለናል እያሉ እንደዳልፎከሩ ሁሉ ዛሬ ባለ ተራ እነሱ ሲሆኑ እኛ በአፍሪካ ገናና ትጥቅ አለን፣ በግሩም ሁኔታ የሰለጠነና የተደራጀ ሰራዊት አለን፣ በሞራል የተገነባ እስካፍንጫው የታጠቀ ወታደር ባለቤት ነን እና ሌሎችንም በመደርደር የትጥቅ ትግልን አትሞክሩት ሊሉን እየዳዳቸው ይገኛሉ። ምክንያቱም ወያኔዎች ሁሌም ልዩዎች ናቸዋ። ነገሩ ሁሉ ለነሱ ብቻ እንጅ ለሌሎች አየሳካማ። ከዚህ በላይ የደከመ አስተሳሰብ የተልፈሰፈሰ አመለካከት ከወያኔዎች በቀር ማን ሊያቀርብ ያችላል?
በሌላ በኩል ደግሞ ቅድም እነ እንቶኔ ፈጠሩትና ረዱት ያለውን ረስቶ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይልን ከግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ጋር በማቆራኘት ይህ ንቅናቄ ተከፋፍሏልና ጠንካራ ወታደራዊ ሃይል ሊፈጥር አይችልም ይለናል ወያኔ። እርግጥ ነው ባንድ የትጥቅ ትግል በሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ስም ብቻ በየሩብ ዓመቱ የራሱን ምናባዊ አንጃ እየፈጠረ ሲታረቅ ለኖረውና ይህኑ ሪፖርት ሲያደርግ ለቆየው ወያኔ ይህ ምንም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሀቅን እንዳለ ለማስቀመጥ እንደሚሞክር ኢትዮጵያዊ ዜጋ ግን ስለ ግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል ያየነው ድረ ገፃቸውን፣ የበተኑትን የመጀመሪያ መግለጫና ኢሳት ላይ ተወካያቸው በድምጽ የሰጠውን ቃለ ምልልስ ብቻ ነው። ከነዚህ ባንዱም ላይ የግንቦት 7 ንቅናቄ አካል ነን አላሉም። ወያኔና ትግራይ ኦን ላይን ግን በዚህ ጉዳይ የተነሳ ገንፍለው አካባቢ ሊበክሉ እየሞከሩ ነው። እንደተለመደው ያልታየውን እያዩ የማይሰማውንም እየሰሙ ያለ ድካም እያወሩ ይገኛሉ።
ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉ ጉዞውን ቀጥሏል ነውና ግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል ተቀባይነትን እየገኘ በሰው ሃይል በእቃ አቅርቦት በሞራል እንዲሁም በማንኛውም መልኩ ሕዝባዊነቱን ለማሳየት ጠንክሮ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ በሚታመንበት በዚህ ሰአት ወያኔዎች ግን በራሳቸው ዓለም ልክ በትግራይ ኦን ላይን ላይ እንደታየው ታምሰዋል። በመላ ምትና በስማ በለው ያለ ድካም እያወሩ ቀጥለዋል። ልብ ይስጣቸው ማስተዋልን ያድላቸው አትሉልኝም። አበቃሁ።
No comments:
Post a Comment