Sunday, November 25, 2012

ላፍቶን አደራ


ለወትሮዉ እንኳን ልቅሶና ኡኡታ ሹክ የሚል ድምጽም ደጋጋግሞ የማይሰማባት ላፍቶ በህፃናት፤በሴቶችና በአረጋዉያን የሰቆቃ ጩኸት እየተተራመሰች ነዉ። እናት የመንፈቅ ልጇን ታቅፋ እንዳታጠባዉ እሷ እራሷ ምግብ ከቀመሰች ሁለት ቀኗ ነዉና ጡቷ ደርቋል፤ እንዳታስተኛዉ ቤቷን የወያኔ ቡልዶዘሮች እንዳልነበረ አድርገዉታል።  አባት ሁለት ልጆቹን ታቅፎ አዉላላ ሜዳ ላይ ተኝቷል፤ ልጆቹ ቢነቁ የሚጠይቁትን የዉቃልና ቀኑን ሙሉ ቢተኙ ደስ ይለዋል። እሱም ቢሆን አንኳን የሚበላ “የሚላስ የሚቀመስ” የለዉምና ያለዉ አማራጭ መተኛት ብቻ ነዉ። ምግብ ወይም ስራ ፍለጋ እንዳይሄድ የእሱም መኖሪያ ቤት በወያኔ ቡልዶዘሮች ስለተናደ ሁለት ልጆቹን ጥሎ ዬትም መሄድ አይችልም።  የአዲስ አበባ ዉርጭ ሲነጋጋ ያንገበግባል፤ ቀን የፀሐዩ ሙቀት አታምጣ ነዉ፤  ሲመሽ ደግሞ ብርዱ ዛር እንደያዘዉ ሰዉ ያንቀጠቅጣል። ላፍቶ ዉስጥ ልብስ የለም፤ምግብ የለም መጠለያም የለም። እመጫት የመንፈቅ ልጇንና ባዶ ሆዷን ታቅፋ አባት ደግሞ ሁለት ልጆቹን ግራና ቀኝ አስተኝቶ ሁሉም  ጧት በዉርጭ፤ ቀን በሀሩር ማታ ደግሞ በብርድ ይጠበሳሉ። ይሄ ሁሉ የፍጥረት ሰቆቃ የሚታየዉ አዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዉስጥ ነዉ። ላፍቶን የመንግስት ጭካኔ፤ የከንቲባዋ ዝምታና የኗሪዎቿ  ጨኸት እረፍት ነስቷታል።  አዎ! ላፍቶ በአንድ በኩል በቡልዶዘር ጩኸት፤በሚፈርስ ቤት ጩኸትና ህዝቡን በሚያሸብሩ የፌዴራል ፖሊሶች ጩኸት በሌላ በኩል ደግሞ በህፃናት ልቅሶ፤ በአባቶች ኡኡታና በሴቶችና በአረጋዉያን ጩኸት ተወጥራለች። በንጉስ ሄሮድስ ዘመን “ጩኽት በራማ ተሰማ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ ዉስጥ እንደተጻፈ ዛሬም በወያኔ ዘመን ጩኸት በላፍቶ ተሰማ።
ብዙ ህዝብ የሚኖርባት ላፍቶ በወያኔ ዘመን ከተስፋፉት የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች አንዷ ናት። እንደማንኛዉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ላፍቶም ደሀዉ ጎጆዉ ቀልሶ ሀብታም ቪላ ገንብቶ ጎን ለጎን እየተያዩ የሚኖርባት ቦታ ናት። አቅም ካለዉ ላይና ታች አለዚያም  እንደአቅምቲ ዛኒጋባዉን ተክሎ የሚኖረዉ የላፍቶ ነዋሪና በፌዴራል ፖሊስ ቪላዉ የሚጠበቅለት የቦሌ ነዋሪ ሁለቱም እኩል ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ። ፌዴራል ፖሊስ ዘራፊዎቹን የወያኔ ሹማምንት እቤታቸዉ ድረስ አጅቦ እያስገባ የላፍቶዉን ደሃ ደግሞ ቤቱን የሚያፈርስበት ምንም ምክንያት የለም። የከተማ ፕላን ወጥቶ ከተማ የሚገነባዉ ለህዝብ ህንጻዎች የሚሰሩትም ሆነ የሚፈርሱት ለህትዝብ ትቅም ሲባል ብቻ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ዬትም አገር ዉስጥ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት የሚጻረር ምንም ነገር አይሰራም ወይም አይፈርስም። ይህ በብዙ አገሮች ዉስጥ የሚሰራ ህግ ወያኔ በሚመራት ኢትዮጵያ ወስጥ አይሰራም። ኢትዮጵያ ዉስጥ የህዝብ ጥቅም ቢነካ ባይነካ የወያኔ ባልስልጣኖችና ጓደኞቻቸዉ አይን ያረፈበት ቤት ወይም ህንፃ ሰበብ ተፈልጎለት ይፈርሳል። የወያኔ ካድሬና ሹም ካልፈለገዉ በከፍተኛ ወጪ የተሰራ መንገድ ይፈርሳል ወይም መሰራት የሌለበት መንገድ ይሰራል።
በቅርቡ የወያኔ ግፈኞች አላግባብ ቤት ሰርታችኋል ብለዉ ቤታቸዉን የፈረሱባቸዉ አባ ወራዎች ብዛት ለ17 ሺ ባላይ ነዉ፤ ይህ ቁጥር ደግሞ አባ ወራዎቹን ብቻ አንጂ እናቶችን፤ህጻናትንና የቅርብ ቤተሰብ አባላትን አያጠቃልልም። በፊዉዳሉ ስርአት ዉስጥ የመሬት ከበርቴዉ የጭሰኛዉን ጎጆ አፍርሶ የራሱን ይዞታ እንደሚያስፋፋ ሁሉ ዛሬም ወያኔ የከተሜዉን ቤት እያፈረሰ ቦታዉን የኔ ለሚላቸዉ ስግብግቦችና ለሆዳችዩ ላደሩ ምስለኔዎች እየሰጠ ነዉ። ወያኔ እንደለመደዉ ቤቱ የተሰራዉ ከህግ ዉጭ ነዉ እያለ ቢዋሽም በታቸዉ የፈረሰባቸዉ ሰዎች አንደተናገሩት ቤታቸዉን የሰሩት መንግስት ፈቅዶ ነዉ ወይም ቤቶቹ ሲሰሩና ተሰርተዉ አልቀዉ ቅዶ ነዉ ወይም ቤቶቹ ሲሰሩና ተሰርተዉ አልቀዉ ነዋሪዎቹ ሲገቡ ነዋሪዎቹ ሲገቡ ወያኔ ያዉቅ ነበር።  ባያዉቅስ? መንግስት ደፈርከኝ ብሎ ህዝብን የሚበቀል አካል አይደለም። የ60 ሺ ዜጎችን መኖሪያ ቤት አፍርሶ ነዋሪዎቹን ሜዳ ላይ የሚበትን መንግስት እንኳን ኢትዮጵያ ዉስጥ በአለማችንም የታየዉ በአፓርታይድ ደቡብ አፋሪካና በቀድሞዋ ሮዴሺያ ዉስጥ ብቻ ነዉ። እነዚህ ሁለት አገሮች ደግሞ ዘረኝነት የነገሰባቸዉ አገሮች ነበሩ። ይህንን ያክል ህዝብ ለአገር ጥቅም ሲባል መፍረስ ካለበት በመጀመሪያ ዜጎቹ የሚኖሩበት ቦታ ተፈልጎ መገኘት አለበት እንጂ የሰዉ ልጅ እንደለማዳ እንስሳ ከመኖሪያ ቤቱ ተገፍቶ ወጥቶ አይኑ እያየ መኖሪያ ቤቱ በቡሉዶዘር አይናድም። ለማዳ እንስሳ እንኳን ሌላ ቤት ይሰራለታል እንጂ ባዶ ሜዳ ላይ አይጣልም። ወያኔ ዘረኛ ነዉ የሚባለዉ ለካስ እንደዚህ የኔ አይደሉም የሚላቸዉን ዜጎች ከእንስሳ አሳንሶ ስለሚያይ ነዉ።
ወያኔ ስሙ በተነሳ ቁጥር የሚዘገንነን ጭካኔዉ ብቻ አይደለም። ምንም አይነት የህዝብ ስሜት የማይገባዉና ለሀዝብ የሚያዝን ልብ የሌለዉ የደነዞች ስብስብ መሆኑ ነዉ።  በቅርቡ ላፍቶ ዉስጥ ፖሊስ ወላጆቻቸዉ ፊት በዱላ ቀጥቅጦ የገደላቸዉ የሁለት ህጻናት አሳዛኝ ሞት የሚያሳየን ይህንኑ የወያኔ ጭካኔና ለአገርና ለህዝብ የሚያሳየዉን ግድየለሽነት ነዉ። ለወትሮዉ “በአቡዬ” ና “በማሪያም” ስም የሚማጸነዉ የላፍቶ ህዝብ እነዚህ ደነዞች ቢገባቸዉ ብሎ የዚያን የደሃ አባት ተብሎ የተነገረለትን መሪ ፎቶ በደረቱ ታቅፎ ነበር የለመናቸዉ፤ ችግሩ የቤታቸዉ መፍረስና የእነሱና የልጆቻቸዉ መንገላታት የዚሁ ፎቶዉን የተሸከሙት ሰዉ ራዕይ ስለሆነ የሚሰማቸዉ ጠፋ።

ኃ/ማሪያም ደሳለኝም ቢሆን ለመለስ ዜናዊ ራዕይ ግብ መምታት ቆርጦ የተነሳ ሰዉ ስለሆነ እንኳን የህዝብን ጩኸት ሰሞኑን በተደጋጋሚ ስሙን ያነሳዉን ፈጣሪ ድምፅም የሚሰማ አይመስልም።  የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳም ቢሆን ስማ ተብሎ የተነገረዉን ብቻ እንጂ ከትዕዛዝ ዉጭ ምንም ነገር የሚሰማ ጆሮ የለዉም።  ፈጣሪም ቢሆን ከላይ ሆኖ ይመለከታል እንጂ በታላቅ ስሙ ስላልተለመነ አይሰማቸዉም። ታዲያ የላፍቶን ህዝብ ጩኸትና ልቅሶ ማን ይስማ?
ላፍቶ ዉስጥ ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉ ከ30 ሺ በላይ አባወራዎች ባለፈዉ ሳምንት ከንቲባዉ ቢሮ በዚህ ሳምንት ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ቀርበዉ አቤቱታቸዉን ማሰማት ቢሞክሩም ከጠ/ሚኒስትሩም ሆነ ከከንቲባዉ የተሰጣቸዉ ምላሽ በፓሊስ መደብደብና መታሰር ብቻ ነበር። ዛሬ በየመንገዱና በየአደባባዩ ተበታትነዉ የሚኖሩት የላፍቶ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ሁሉም ተማሪዎች ናቸዉ፤ ሆኖም እነዚህ ተማሪዎች ዛሬ እንኳን ት/ቤት ሊሄዱ ገላቸዉን ታጥበዉ ልብስ የሚቀይሩበት ቦታ የላቸዉም። የሚገርመዉ እነዚህ ወጣቶች ተወልደዉ ያደጉት ዛሬ ወያኔ ህገወጥ ናቸዉ ብሎ ባፈረሳቸዉ ቤቶች ዉስጥ ነዉ። እነዚህ ቤቶች ከአስር አመት በላይ የቤት ግብርና የኤሌክትሪክ ፍጆቻ ሂሳብ የተከፈለባቸዉ ቤቶች ናቸዉ። ዘረኞቹ የወያኔ ገዢዎች ሊነግሩን እንደሚሞክሩት የፈረሱት ቤቶች ህገወጦች ከሆኑ እንዴት መብራት ገባላቸዉ? እንዴትስ የመንግስት ግብር ሰብሳቢዎች አወቋቸዉ? ቤቶቹ ህግወጦች ናቸዉ ብለን ብናምን እንኳን ምን አይነት መንግስት ነዉ ከ30 ሺ በላይ አባወራዎችንና ቤተሰቦቻቸዉን ሜዳ ላይ በትኖ ቤታቸዉን የሚያፈርሰዉ? ለዚያዉም ወያኔን የመሰለ 99.6%  የህዝብ ድምጽ አገኘሁ ብሎ የሚፏልል መንግስት!
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ በወያኔ ዘረኞች ሰብዓዊ መብቱ ያልተረገጠ ዜጋ ወይም ወያኔ ያላዋረደዉ የህብረተሰብ ክፍል የለም። ወላጆች ልጆቻቸዉ ፊት ተገድለዋል፤ ህፃናት ከእናቶቻቸዉ እቅፍ ተነጥቀዉ በዱላ ተቀጥቅጠዋል። ወጣት ተማሪዎች ለምን ሠላማዊ ሠልፍ አደረጋችሁ ተብለዉ በአደባባይ ተረሽነዋል። ጋዜጠኞች ለምን ጻፋችሁ ተብለዉ ታስረዋል፤ ተደብድበዋል ከአገር ተሰድደዋል። ከወያኔ ጋር ንኪኪ የሌለዉ ነጋዴ የንገድ ፈቃዱ ስለማይታደስ ከስሮ ንግዱን ዘግቷል። ከወያኔ ካድሬዎች ጋር የማይተባበር ገበሬ የማዳበሪያ፤የምርጥ ዘርና የፋይናንስ አገልግሎት ስለሚከለከል በገዛ አገሩ ባይተዋር መሆኑን ጠልቶ ወደ ጎረቤት አገሮች እየተሰደደ ነዉ። የአህአዴግን የአባልነት ፎርም አንሞላም ያሉ ሰራተኞች ከስራቸዉ ተባርረዋል። በዘረኛ የህወሀት መኮንኖች የሚታዘዘዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምድር ሲኦል ሆኖበታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ጥቂት ዘረኞች እየረገጡ ሊገዙን 17 አመት መስዋዕትነት የከፈሉ ከሆነ የእኛ 21 አመት ሙሉ አንገት ደፍቶ መገዛት ከዉርድም ዉርደት ነዉ። እነሱ በዘር ከፋፍለዉ ሊገዙንና አገራችንን ሊበታትኑ የከፈሉትን መስዋዕትነት እኛ የአገራችንን አንድነት ለመጠበቅና ነፃነታችንን ለማስከበር የማንከፍልበት ምንም ምክንያት የለም። የዛሬዉ የወያኔ ግፍ ሰለባ ላፍቶ ስለሆነች እንደምሳሌ አቀረብናት እንጂ የእነዚህ ዘረኞች ግፍና በደል የጀመረዉ እግራቸዉ አዲስ አበባን የረገጠ ቀን ነዉ። አርሲና ሐረር ዉስጥ ሲጨፈጭፉን ዝም አልናቸዉ . . . አኝዋክ ላይ ደገሙን። አኝዋክ ላይ በአንድ ጀምበር ከ400 ሰዉ በላይ ሰጨፈጭፉ ዝም አልናቸዉ አምቦና  አዋሳ ላይ መጡብን። ሐረር፤ አርሲ፤ ጋምቤላ፤ አምቦና አዋሳ ላይ ህዝብ እንደ እንስሳ ሲታረድ እኛም ሆንን አለም አቀፉ ህብረተሰብ ያሳየዉ ዝምታ የልብ ልብ ሰጥቷቸዉ የአዲስ አበባን መንገዶች የዉግያ ወረዳ አስመስሏቸዉ። ይህንን ሁሉ ግፍና በደል ያደረሰብን ግለሰብ ዛሬ በህይወት ባይኖርም እሱን የተካዉ ሰዉ የእሱን ራዕይ ለማስፈጸም የቆረጠ ሰዉ ነዉና ይሀ ዘረኛ ሰዉ የጀመረዉ ግፋና ጥፋት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።
ቱኒዝያ፤ ግብፅ፤ ሊቢያና የመን ዉስጥ አምባገነን መሪዎችን ጠራርጎ ያጠፋዉ የአረቡ አብዮት ቱኒዝያ ዉስጥ ሲፈነዳ የቱኒዚያን ህዝብ በቃ ብሎ ያነሳሳዉ የመሐመድ ቦአዚዝ መስዋዕትነት ነዉ። እኛ አንድ መሐመድ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ መሐመዶችን ሰዉተናል። የኔሰዉ ገብሬና ጓደኛዉ ግርማ ወ/ማሪያም እንደ መሐመድ ቦአዚዝ እራሳቸዉን ሰዉተዋል። መሀል አዲስ አበባ ዉስጥ 200 ሰዎች ዉድ ህይወታቸዉን ሰጥተዉናል; አሁን በቅርቡ ደግሞ ወሎ ዉስጥ የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞቻችን መሲጊድ ዉስጥ ተገድለዋል። ወያኔዎች ይህ ሁሉ አልበቃ ብሏቸዉ ከሰሞኑ የላፍቶን ነዋሪ ቤቱን እላዩ ላይ አፍርሰዉ ሁለት ገና በእግራቸዉ ቆመዉ መሄድ ያልጀመሩ ህፃናትን ከወላጅ እናታቸዉ እቅፍ ነጥቀዉ በዱላ ደብድበዉ ገድለዋል። ታድያ ከዚህ በላይ ምን እስኪያደርጉን ድረስ ነዉ የምንጠብቀዉ?  ይህ ዝምታ የጤና አይመስልም . . . . እንኳን ሰዉ ወተተም ሲበደል ይሸፍታል።
ከሁለት አማራጮች አንዱን መምረጥ የግድ ነዉ። ታግሎ ነፃ መዉጣት ወይም እየተገዙ መኖር። ለነጻነት የሚከፈለዉ ዋጋ ምን ግዜም ቢሆን ትልቅ ነዉ ሆኖም የየዘመኑ ኢትዮጵያዉያን ይህንን ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ አልፈዋል። ዛሬ የኛ ተራዉ የኛ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዉያን የማንመርጠዉ አማራጭ ቢኖር በቃኝ ብሎ እጅ መስጠትን ወይም ተሸንፎ መኖርን ነዉ። እነሱ ጥቂቶች እኛ ብዙኋን ነን። እነዚህን ዘረኞችና የገነቡትን ስርአት ለመደምሰስ የብዛታችንን ያክል መሰለፍ የለብንም። የሚያሰፈልገን አንድ ነገር ብቻ ነዉ እሱም በገጠርም በከተማም ለወያኔ አልገዛም ማለት ብቻ ነዉ፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከአሁን የተሻለ ግዜ የለምና በአንድ ላይ እንነሳ!

No comments:

Post a Comment