ኢሳት ዜና:-ከአመት በላይ በቃሊቲ እስር ቤት ታስሮ የተፈታው ዮሃን ፐርሹን ይህን ያስገነዘበው ትናንት ባለፈው ሳምንት በስቶክሆልም ስዊድን ከተማ በሚካሄደው ዓመታዊው ታላቁ የስዊድሽ ጋዜጠኞች ሽልማት ስነስርዓት ላይ ሲሆን በዚሁ ወቅት እሱና ባልደረባው ማርቲን ሺብዬ ከእስር ተፈተው በነጻነት እንደልባቸው ለመንቀሳቀስ ቢችሉም በአሁን ሰዓት በቃሊቲ እና በሌሎች እስር ቤቶች በመማቀቅ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን የህሊና እስረኞች ጉዳይ እጅግ እንደሚያሳስባቸው ተናግሯል።
በቃሊቲ ታስረው የሚገኙ ጋዜጠኞች ወንጀላቸው መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎችን በመጻፋቸው ብቻ ነው፡እነዚህ የህሊና እስረኞች በአሸባሪነት ተከሰው እስከ 20ዓመት የሚደርስ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞቿን እንዲሰደዱ በማድረግ በግንባርቀደምትነት ተጠቃሽ ነች።
በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእኛን እስር በተመለከተ በአማርኛ በመጻፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ህብረተሰብ ግንዛቤ እንዲያገኝ ያደረጉት ጥረት መቼም አንዘነጋውም። ስዊድን ጋዜጠኞችን ወደ ቃሊቲ ከመላክ እንድትቆጠብ እጠይቃለሁ በማለት በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ለተገኙት ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተወካዮች የችግሩን አሳሳቢነት አመልከቷል።
ከሽልማቱ ስነስርዓቱ ማብቂያ በኋላ በሰጠው ቃለምልልስ እሱና ባልደረባው ይግባኝ ያልጠየቁት በኢትዮጵያ ባለው የፍትህ ስርዓት እምነት ስሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ የእነእስክንድር ነጋን ይግባኝ ለማየት ከተቀጠረው ችሎት ምንም የተለየ ነገር እንደማይጠብቅ ገልጿል።
ባልደረባው ማርቲን ሺብዬ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት በእለቱ ቪየና ኦስትሪያ ዩኔስኮ በግጭት ክልሎች የሚገኙ ጋዜጠኞች ደህንነት እንዴት መከላከል እንደሚቻል ለመወያየት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ በመገኘት ኢትዮጵያ ውስጥ ለ14 ወራት በታሰሩበት ወቅት ስላሳለፉት ስቃይ እና መከራ እንዲሁም በውሸት ማስረጃ ስለተከሰሱበት የፍርድ ሂደት ለተሰብሳቢዎቹ ማስረዳቱንና የስብሰባው ተሳታፊዎች በሁኔታው እጅግ መገረማቸውንና ማዘናቸውን ገልጿል።
አብዛኛው ህብረተሰብ እኔ እና ዮሃን ከተፈታን በኋላ በኢትዮጵያ ያለው ችግር እንደተቃለለ ይገምታል ነገርግን አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ የጸረሽብርተኝነት ህጉ አሁንም በስራ ላይ ሲሆን በሱም የተነሳ ብዙ ጋዜጠኞች በእስር ላይ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚካሄደው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተባባሰ ነው። ከዚህም በመቀጠል እሱና ማርቲን ቃሊቲ እስር ቤት ለሚገኙ ጓደኞቻቸው የገቡትን ቃልኪዳን በመጠበቅ በተገኘው አጋጣሚ ዓለምዓቀፉ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማድረግ እነዚህ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚያደርጉትን ትግል እንደሚያጠናክሩና በመጽሃፍ መልክ የሚታተተመው የእስርቤት ቆይታቸው በአማርኛ ተተርጉሞ ለኢትዮጵያውያን በነጻ እንዲያነቡት የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቋል በማለት ቴውድሮስ አረጋ ከስዊድን ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment