የሰው ልጅ መብትና ነጻነት ከእግዚአብሔር ያገኘው ነጻ ሥጦታ እንጂ መስቀልም ሆነ ጠመንጃ በያዙ ሰዎች ችሮታ የሚታደለው አይደለም!!
አባ ግርማ ከበደ
“በእኔ በኩል ይህንን የቤተ ክርስቲያንን ንብረት ይይዛል የሚባለውን ካምፓኒ እስከተው ድረሥ ሌላውን ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ” መሪጌታ ዓለማየሁ ደስታ“ጽላቱም ሆነ ንብረቱ በእጃችን ስለሚገኝ ይህ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የሚሉት ይሸጥና ድርሻችንን ወስደን ሌላ ቤተ ክርስቲያን እንመሠርታለን”
ከላይ የተመለከተው የሁለቱ ካህናት ንግግርና ገለጻ የተደመጠበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ሁለቱም ካህናት መግለጫውን የሰጡት ዓርብ 15 February 2013 ሲሆን አባ ግርማ ከበደ የተናገሩት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረውን የሰላም መታጣት አስመልክቶ መፍትሔ ለማስገኘት የሚጥሩ ሰዎች ሲያነጋግራቸው ሲሆን፤ መሪጌታ ዓለማየሁ ደግሞ ንግግሩን ያደረጉት በተመሳሳይ ዕለት በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ደጋፊዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን የተወሰኑ ካህናት፤ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በድብቅ ሰብስበው የተንኮል ዕቅድ በሚሸርቡበት ወቅት ነው።
ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ፡
ሰራተኛው ለፍቶና ጥሮ፤ ግሮ ከሚያገኘው ደምወዙና ገቢው፤ ሥራ የሌለው፤ ጡረተኛ፤ አቅመ ደካማና ልጅ አሳዳጊ ደግሞ ከሚያገኘው ድጎማና ጡረታው ላይ በመቀነስ የኦርቶዶክስ
ሃይማኖቱ ማዕከልና የሃገሩ ኢትዮጵያ ምትክ አድርጎ ለሚያያት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመለገስ ሁሉም ባደረጉት እጅግ የሚያኮራ መረባረብ £1.7 ሚሊዮን ፓውንድ በማውጣት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ትልቅ የመኖሪያ ሕንፃ ገዙ።
ከዚህም በተጨማሪ ጊዜአቸውን፤ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ያለ አንዳች ጥቅምና ክፍያ ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት በማበርከት በከፍተኛ መስዋዕትነት ቤተ ክርስቲያኗን አሁን ለደረሰችበ የዕድገት ደረጃ ካበቋት በኋላ ዛሬ ባለቤቶችና በቤተ ክርስቲያኗ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝኞቹም ሆኑ ተደራዳሪዎቹ አባ ግርማ ከበደና መሪ ጌታ ዓለማየሁ ሆነዋል።
ይህ ብቻም አይደለም ለአባ ግርማም ሆነ ለመሪ ጌታ ዓለማየሁ በድምሩ በወር ከ£2.300 ፓውንድ በላይ ደምወዝ የሚከፍለውና ለሌሎችም አገልጋይ ካህናት ደምወዝ እየከፈለ የሚያኖራቸው ይኸው መኖሩንም ሊረሱት የሚሞክሩት ሕዝብ ነው።
እነ አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው ግን ይህንን ሃቅ ንቀው በመተው ካህናት ስለሆንን ብቻ ለሕዝቡ የፈለግነውን የሃሰት ወሬ ብንነግረው አምኖ ይከተለናል በሚል እብሪት በመሞላት በሕዝቡ ውስጥ የሃሰት ወሬና ማስፈራሪያ እየነዙ ሕዝቡን ከፋፍለውና አበጣብጠው በቤተ ክርስቲያኗ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ ከነሱ ሌላ ማንም ወሳኝ እንዳይኖር ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛሉ።
በእርግጥ ሕዝበ ከርስቲያኑ ለሃይማኖቱና ለቤተ ክርስቲያኑ ባለው ታላቅ ፍቅርና ከበሬታ አንጻር ካህናቱ በሚነዙት የሃሰት ወሬ በመወናበድ የተወሰነው ክፍል ለጊዜውም ቢሆን የነሱ መሣሪያና መጠቀሚያ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ አዳጋች አይሆንም፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የማትሞተውና ተቀብራ የማትቀረው እውነት ጎልታ እስከምትወጣ ድረስ ብቻ ነው።
ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ካህናቱ “ቤተ ክርስቲያንን ካምፓኒ ሊያደርጓት ነው፤ ይህም ከክርስቶስ ይለየናል፤ ቆኖና ይፈርሳል” ወ.ዘ.ተ የሚል በሬ ወለደ ውሸትን በማስወራት በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ሽብርን ይነዛሉ። ይህ ግን በእርግጥ እውነት ነው?
ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ሃገር የቻሪቲ ሕግ መሠረት Charitable Trust (የምግባረ ሰናይ ተቋም) ነች። ይህ የሆነበት ምክንያትም ቤተ ክርስቲያኗ በቻሪቲ ኮሚሽን ተመዝግባ የቻሪቲ ቁጥር ካላገኘች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ለመቀጥል የሚያስችላትን ከታክስ ነጻ የሆነ ገንዘብ ከሕዝብም ሆነ ከሌላ አካል ማሰባሰብ ስለማትችል ነው።
ይህም ብቻ አይደለም ቻሪቴብል ትረስት በመሆኗ ከመንግሥት የGift Aid እና ሌሎች ድጎማዎችን የማግኘት መብትን ያስገኝላታል።
ታዲያ ቤተ ክርስቲያኗ ቻሪቴብል ትረስት ከሆነች፤ ቻሪቲ ደግሞ አትራፊ ያልሆነ የበጎ አድራጊ ድርጅት ማለት ከሆነ፤ እንዴት ብሎ ካምፓኒ ወይም አትራፊ የንግድ ድርጅት በመሆን ሁለት ተጻራሪ ነገሮች አንድ ይሆናሉ? (እዚህ ላይ ነው ካህናቱ የሕዝቡን እውቀትና የማገናዘብ ችሎታ እጅግ ዝቅ አድርገው በማየት አይንህን ጨፍንና እናሞኝህ የሚሉት)
ቤተ ክርስቲያን ያህል ቀርቶ ግለሰብም ቤት ገዝቶ ባለቤትነቱን ለሌላ ሰው በአደራ ልስጥ አይልም። አይደለም ቤትን ያህል ነገር ቴሌቪዥንም ሆነ ከዛ ያነሰ ዕቃ እንኳ ቢሆን ገዝቶ በሌላ ሰው ስም በአደራ ይያዝልኝ ብሎ የሚመርጥ ሰው የለም።
በአሁኑ ወቅት ግን በ£1.7 ሚሊዮን ፓውንድ የተገዛው የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ንብረት የተያዘው በ4 ሰዎች ስም ነው። ይህ ለምን ሆነ? ለምንስ ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ስም ንብረቷን መያዝ አልቻለችም?
በUK የመሬትና የንብረት ይዞታ ሕግ መሠረት እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ያለ ቻሪቴብል ትረስት ያለውን ቤት መሬትና ንብረት ለሰውም ሆነ ለመንግሥት በአደራ ከማስያዝ ይልቅ በራሳቸው ሥም መያዝ የሚችሉት ለዚሁ ተብሎ በተቋቋመው Charitable Company Limited by Guarantee የሚባልን በማቋቋም ብቻ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም የእኛን ቤተ ክርስቲያን የመሰሉና ሌሎችም በቻሪቲ ኮሚሽን የተመዘገቡ ድርጅቶች ንብረታቸውን በስማቸው ለመያዝ ሲሉ በCompany House መመዝገባቸውን ለማቃለል ሲባል በራሱ በቻሪቲ ኮምሽን ሥር ሆነው ንብረት በስማቸው የመያዝና ሕጋዊ ሰውነት የማግኘት መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል Charitable Incorporated Organisation (CIO) የሚል የሕግ ረቂቅ ቀርቦ ውሳኔው ለ6 ዓመት ከተጓተተ በኋላ ከ2012 መጨረሻ ጀምሮ በፓርላማ ሕግ ሆኖ በመጽደቁ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ካምፓኒ ሃውስ መመዝገብ ሳያስፈልጋት በቻሪቲ ኮምሺን ሥር ባለው በCIO ሥር በመመዝገብ ንብረቷን በስሟ መያዝና በስሟ ሕጋዊ ሰውነትን (Legal Entity) ማግኘት ትችላለች። ይህንን ግን አንዳንድ ካህናት ሳያውቁት ቀርተው አይደለም ሕዝብን የማያውቅና የማያገናዝብ አድርገው በማየት እንጂ።
እንዴትስ አድርጎ የቤተ ክርስቲያን ንብረት በግለሰቦች ስም በአደራ መያዝ፤ ቀኖና የሚፈቅደው ሆኖ ቤተ ክርስቲያን ንብረቷን በራሷ ሥም መያዝ ቀኖና የሚያፈርስና ከክርስቶስ የሚያለያይ ይሆናል? ይህም ቢሆን ደግሞ ሕዝብ የቀረበለትን የሕግ ረቂቅ አይቶና መርምሮ ይሁን፤ አይሁን፤ ይለወጥ ወይም ይሻሻል፤ ይቅር፤ ይለፍ ይላል እንጂ ከህዝብ ውጪ ይሁን አይሁን የሚል ውሳኔና ፍርድ የመስጠት መብት የጥቂት ካህናት ይሆናል።
ሕዝብ የቤተ ክርስቲያኑ አዛዥና ወሳኝ መሆኑን አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው የሚቀበሉ ከሆነ ለምን ሕዝብ በረቂቁ ላይ ተወያይቶ እንዳይመርጥና እንዳይወስን አሰናከሉት? ለምን በሃሳብ መስጫ ሳጥን ያስገባው አስተያየት ሳይነበብ እንደተዘጋበት እንዲቀር አደረጉት? ለምን በውይይቱ ወቅት የምእመኑ ተራ ሲደርስ ውይይቱን በረብሻ አስቆሙት?
ካህናቱ ሌላው ቢቀር Charitable Company Limited by Guarantee ከሚለው መጠሪያ ውስጥ Charitable የሚለው የመጀመሪያው ቃል ብቻ አትራፊ የንግድ ድርጅት ለሚለው አፍራሽ እንደሆነ መረዳት የሚያቅተው ሰው ይኖራል በማለት ሕዝብን ለማታለል መሞከራቸው በእጅጉ የሚገርም አይደለም?
አባ ግርማ ከበደና መሪ ጌታ ዓለማየሁ በተለየ ሁኔታ ይህንን ሁሉ ተንኮል የሚፈጽሙት ለምን ብለውና ምን ለማግኘት ነው?
አባ ግርማ ከበደ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት በመያዣነት ይዤ እቆያለሁ የሚሉት ቤተ ክርስቲያኗን አሳልፈው በመስጠት በአጸፋው የጵጵስና ሹመትንና የደለበ ጥቅምን ሊያስገኝ የሚችል ሥልጣንን ለማግኘት ነው። ይህንን የመሰለ ታሪክ ሩቅ ሳንሄድ አባ ጳውሎስን ሲያወግዙና ሲኮንኑ ኖረው በመጨረሻ ከአባ ጳውሎስ የጵጵስና ሹመት ተቀብለው በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ክህደት በመፈጸም አሳልፈው የሸጡት የሰሜን አሜሪካውን አባ መላኩን ማስታወስ በቂ ነው።
መሪ ጌታ ዓለማየሁ ደስታ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗም ሆነች ንብረቷ የቅዱስ ሲኖዶስና የመንበረ ፓትሪያርክ ነች በሚል ሽፋንና ቤተ ክርስቲያኗ ተሸጣ እንካፈል በሚል ሃሳብ ሕዝቡ ተከፋፍሎ እንዲበጣበጥ በማድረግ በዚህ ግርግር እሳቸው ከቤተ ክህነት ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጠቀም ቤተ ክርስቲያኗን በጎን ወስዶ በማስረከብ በምላሹ በሳምንት ከ4 ሰዓት ያልበለጥ ለሚሰሩበት በወር £100.00 (አንድ ሺህ ፓውንድ) የሚከፈላቸው ደምወዝ እንዳይቋረጥባቸውና ከሃገር ውስጥ ቃል የተገባላቸውን የተደላደለ መኖሪያና ሌላም ጥቅማ ጥቅም ለማትረፍ ነው።
ይህንን በመሰለ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኗ ዋልታና ምሰሶ የሆነው ሕዝብ ተንቆና እንደሌለ ተቆጥሮ ቤተ ክርስቲያኗ የጥቂቶችን የስልጣንና የንዋይ ጥም ለማርካት ሲባል መደራደሪያ ሆናለች። አባላትና በአጠቃላይ የማርያም ወዳጆች ሁሉ ይህ ሴራ ከሽፎ ሕዝብ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ያለው የባለቤትነት መብት እስከተረጋገጠበት ጊዜ ድረስ በማንኛቸውም መብትን የማስከበርና ቤተ ክርስቲያናችንን የመከላከል ተግባር ውስጥ ሳንዘናጋ ቀንና ሌሊት እንሳተፍ!! ሕገ ወጥነትን በፍትሕ እንርታ! ክፉን በበጎ እናሸንፍ! የሰላምና የፍቅር አምላክ ሁሌም ከእውነት ጋር ነውና አንዳችም ጥርጣሬ አይግባን!! ኃይል የእግዚአብሔር ነው!
No comments:
Post a Comment