በክልሉ የሚገኙ ዳኞች ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ በሆነ መንገድ ለመስራት አልቻልንም በሚል ነው ስራቸውን የሚለቁት። አምና ከ100 በላይ ዳኞች ስራቸውን የለቀቁ ሲሆን በያዝነው አመት ደግሞ ቁጥሩ በእጥፍ ጨምሯል።
ከአንድ ወር በፊት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ታደለ ነጊሾና አቶ ሰይድ ጁንዲን ስልጣናቸውን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲለቁ ከተደረጉ በሁዋላ፣ ችግሩ መባባሱ ተገልጾአል።
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች አሁን ባለው የፌደራል ስርአትና በክልሉ መንግስት ላይ አመኔታ ስለሌላቸው ከስልጣን እንዲለቁ መደረጋቸውን ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ዳኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር140/99 ፕሬዚዳንቱና ምክትሉ ከስልጣን የሚወርዱት በፈቃድ፣ በህመም ፣ በጡረታ ወይም ቅሬታ ካለ ቅሬታው ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ቀርቦ አስፈላጊው ማጣራት ከተደረገ በሁዋላ መሆኑን ቢደነግግም፣ አቶ ታደለና አቶ ሰይድ እንዲወርዱ የተደረገበት አካሄድ ግን ከዚህ የተለየ ነው ብለዋል።
ከሶስት ሳምንት በፊት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ሙዜማም በኦህዴድ አመራር አባልነታቸው የሚታወቁና ገዢውን ፓርቲ ደግፈው በመገናኛ ብዙሀን ሲከራከሩ የነበሩ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በዳኞች ላይ ይፈጸሙ የነበሩት የመብት ጥሰቶች አሁንም ተጠናክረው በመቀጠላቸው ዳኞች ተቃውሞአቸውን ለማሳየት ስራቸውን በገፍ እየለቀቁ ነው።
የአዲሱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሹመት ” ህዝብን መናቅ፣ ህዝብ ምን ይመጣል?” በሚል የተደረገ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ተናግረዋል። “ትናንት ድርጅቴ ኢህአዴግ እንዲህ አድርጎአል እያሉ በሚዲያ ሲናገሩ የነበሩ ሰው ዛሬ ፍትሀዊ ዳኝነት ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም” ያሉት ዳኛው፣ ዳኞች ሃላፊነታቸውን እየለቀቁ ከመሄድ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም ብለዋል።
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የተደረጉት ፕሬዚዳንቱ ፣ የተረከቡትን እቃ አላስረክብም በማለታቸው በደህንንቶች ክትትል ስር እንደነበሩ ለማወቅ ተችሎአል።
በክልሉ የሚታየው ጎሰኝነት እየጨመረ መሆዱም ዳኞች ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑም ታውቋል።
No comments:
Post a Comment