Sunday, January 20, 2013

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን 70 በመቶው የአመራር ቦታ በህወሀት አባለት የተያዘ ነው ተባለ


ግንቦት7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለኢሳት በላከው ሁለተኛ ጥናቱ ላይ እንዳመለከተው በ11 መምሪያዎች የተዋቀረው በስሩ አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱስትሪዎቸን የሚያስተዳደርው የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን አስራ አንድ ትላልቅ መምሪያዎችና አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱሰትሪዎች በዋና ሀላፊነት፤ በዳይሬክተርነትና በምክትል ዳይረክትርነት የሚመሩ በ29 የከፍተኛ አመራር አባላት ነው።
ከእነዚህ 29 ከፍተኛ አመራር አባላት ዉስጥ 69 በመቶዉ ወይም ሃያዉ የህወሀት አባላት የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸዉ።በዚህ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ያላቸዉ ቦታ 31 በመቶ ወይም ከእያንዳንዳቸዉ በቅደም ተከተል ሦስትና ስድስት ሰዎች ብቻ ሲሆን ከተቀሩት አምስት ክልሎች በዚህ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የተመደበ አንድም  ሰዉ የለም ፣ እንደጥናቱ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ እንዱስትሪ ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታል የሚባለዉ የብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን በሲቪልና ወታራዊ መምሪያዎች ተከፋፍሎ የተዳራጀ ሲሆን በስሩ አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱስትሪዎች እንደሚገኙ የጠቀሰው ግንቦት7፣ ከአስራ ሦስቱ እንዱስትሪዎች ዘጠኙን የሚያስተዳድሩት የህወሀት አባላት ናቸዉ። በኮርፖሬሺኑ ዉስጥ ከፍተኛ ስልጣን ከተሰጣቸዉ የህወሀት አባላት መካከል ብረጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘዉ  የብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፖሬሺን ዋና ዳይሬክተር ፤ ኮ/ል ተከስተ ኃ/ማሪያም  በምክትል ዋና ዳይረክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ፕሮዳክሺን ግንባታ ሀላፊ ፤ ኮ/ል ፀጋሉ ኪሮስ በምክትል ዋና ዳይሬክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ወታደራዊ ምርቶች ሀላፊ ፤ ኮ/ል ሙሉ ወ/ሰንበት በምክትል ዋና ዳይረክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ፕሮጀክቶች አስተደዳደር ሀላፊ፤ሻምበል ካህሳይ ክሽን የምርመራና ልማት ዳይረክተርና  ሻምበል ገ/ስላሴ ገ/ጊዮርጊስ የአቅም ግንባታና ስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ይገኙበታል።
ከትግራይ ዉጭ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰቦች በብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን እንዱስትሪዎች ዉስጥ ከፍተኛ የሀላፊነት ደረጃ ባለዉ የአመራር ቦታ ላይ የመቀመጥ ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር አራት ብቻ ናቸው። ኬሚካልና ሴንተቲክ እንዱስትሪ ሃለፊ መ/አ ሰለሞን ዘውዴ፣ አዳማ ጋርመንት እንዱስትሪ ሃለፊ ኮ/ል ፍሰሀ ግደይ፣ ሜታልስ እንዱስትሪ ሃለፊ ሻለቃ መኮንን በላይ፣ ፓወር እንዱስትሪ ሃለፊ፣ ሻምበል አሰፋ የሀንስ፣ ሆሚቹ ኢሚዩኔሽን ኢንጂነሪንግ ሃለፊ ኮ/ል ሀድጉ በላይ፣ ህብረት ማሽን ቱል ኢንጂነሪንግ ሃለፊ፣ ሻምበል ተሰማ ግደይ፣ ቢሾፍቱ አቶሞቲቭ ሎኮሞቲቭ ሀላፊ፣ ኮ/ል ገብረመድህን ገ ስላሴ ፣ የደጀን አቪየሽን እንዱስትሪ ሀላፊ ሳለቃ ኢሉ ጸጋየ እንዲሁም የጋፋት አርማመንት እንዱስትሪ ሀላፊ ሻለቃ ግሩም ገብረመድህን የህወሀት አባላት ትጋረይ ተወላጆች መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል። የኢትዮ ፕላስቲክ እንዱስትሪ ሃለፊ አቶ ጋሻው እምሩ፣ እርሻ መሳሪያዎች እንዱስትሪ ሃለፊ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ እና የሀይቴክ እንዱሰትሪ ሀላፊ ኮ/ል ጸጋየ አንሙት የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ፣ ከኦሮሞ ደግሞ የፋብሪኬንና ስትራክቸራል እንዱስተሪ ሀላፊው ኮ/ል ብቂላ ብቻ ተጠቅሰዋል።
ይህ ጥናት የተጠናዉ ከ2004 እስከ 2005 ዓም ባለዉ የአንድ አመት ግዜ ዉስጥ መሆኑን ተጠቅሷል። ግንቦት7 በቅርቡ በኢትዮቴልኮም ውስጥ ያለውን የብሄር ተዋጽኦ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሰዎቹ የሚሾሙት በዘራቸው ሳይሆን በችሎታቸው ነው በማለት ይከራከራል። መንግስት 7ኛውን የብሄር ብሄራሰቦች ቀን 200 ሚሊዮን ብር በማውጣት በባህርዳር ማክበሩ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment