ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የትግራይን ክልል የአገሪቱ የእንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ዝግጅት ጨርሶ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ባለቤቱ አዜብ መስፍን ይህንኑ በሏ የጀመረዉን የእንዱስትሪ እስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጣ የተነሳች መሆኑን የግንቦት ሰባት ድምጽ ዘጋቢዎች ከአዲስ አበባ በላኩልን ዜና ገለጹ። በዚሁ ዘጋቢያችን አዜብ መስፍን በቅርቡ ለዋልታ ኢንፎርሜሺን ማዕከል የሰጠችዉን ቃለመጠይቅ ዋቢ በማድረግ በለከልን ዜና መሰረት መለስ ዜናዊ ትግራይ ዉስጥ ምን አይነት ፋበሪካዎች አንደሚገነቡ፤ ዬት እንደሚገነቡና ለግንባታ የሚወጣዉ ካፒታል ከዬት እንደሚገኝ የሚጠቁም ሰፋ ያለ ጽሁፍ ጽፎ እንደነበር ያስረዳል።
በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ “የኢትዮጵያ አባት” ተብሎ የተሞገሰዉና ኢትዮጵያን ሃያ አንድ አመት ሙሉ የመራዉ መለስ ዜናዊ ትግራይን ከዘጠኙ የፌዴራል ክልሎች ነጥሎ የአገሪቱ የእንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ሰፋ ያለ እስትራቴጂ ነድፎ የማስቀመጡ ዜና ሲሰማ የመለስ ዜናዊን ራዕይ ከግቡ እናደርሳለን ብለዉ የተነሱትን እነ ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ብዙ የአገዛዙ አባላት እንደተሸማቀቁ ከአዲስ አበባ የሚደርሱን ዜናዎች ይጠቁማሉ።
አዜብ መስፍን በቅርቡ እሷ እራሷ ከምትመራዉ የኤፎርት ኩባንያዎች አንዱ ለሆነዉ ለዋልታ ኢንፎርሜሺን ማዕከል በሰጠችዉ ቃለ ምልልስ መለስ ዜናዊ ከመሰዋቱ በፊት የአምስት አመት የትግራይ እንዱስትሪ በኤፎርት እንዴት መፈጸም እንዳለበት የፃፈዉ እስትራቴጂ እንደነበር ሳታፍር አፏን ሞልታ ተናግራለች። ኢትዮጵያ ዉስጥ “የሙስናዋ እመቤት” በመባል የምትታወቀዉ አዜብ መስፍን በሏ ለትግራይ የነደፈዉን የእንዱስትሪ እስትራቴጂ በዝርዝር ከመናገሯ ባሻገር እሷና ሌሎችም ብዙ ባለስልጣኖች ይህንን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ቀን ከሌት ተግተዉ አንደሚሰሩም ተናግራለች።
ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የኤፎርት ኩባኒያዎች እንቅስቃሴ ደከም ብሎ ታይቶ ነበር ያለችዉ አዜብ መስፍን አሁን ግን የኩባንያዉ እድገት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግራ መስፍን ኢንጅኔሪንግ በያዝነዉ አመት በሦስት እጥፍ ማደጉንና በሚመጣዉ አመት በአምስት እጥፍ እንዲያድግ ለማድረግ ዝግጅቱ መገባደዱን ገልጻለች። ከዚህ በተጨማሪ የዚሁ የኤፎርት ኩባኒያ ንብረት የሆኑት አልሜዳ ጨርቃጨርቅ፤ መሶብ ሲሚንቶና ሱር ኮንስትራክሺን ድርጅቶች በዚህ በያዝነዉ አመት ብቻ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማጋበሳቸዉን ተናግራለች። ኤፎርት ኩባኒያ ህወሀት የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ከሚቆጣጠርባቸዉና ከተለያዪ የአገሪቱ አካባቢዎች ገንዘብና ጥሬ እቃ ወደ ትግራይ የሚያግዝበት ዋነኛዉ መሳሪያ ለመሆኑ በብዙ የአገር ዉስጥና የዉጭ አገር ኤኮኖሚስቶች ተጠንቶ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment