Sunday, October 28, 2012

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) መግለጫ


የገዥው ቡድን ወታደሮች  በደቡብ ወሎ ደጋን እና ገርባ በተሰኙት ከተሞች በሙስሊሙ ማህበረስብ አባላት ላይ በወሰዱት የኃይል እርምጃ ቢያንስ ሶስት ግለሰቦችን ሲገድሉ ሌሎችን ማቁሰላቸው እና ብዙዎችን ደግሞ ለእስር መዳረጋቸው ተረጋግጧል።
የሙስሊሙ ማህበረስብ በገዥው ቡድን በወያኔ/ኢህአዴግ እየተካሄደ ያለበትን ጣልቃ ገብነት ፣ የመሪዎቹን እስራት አና ያላሰለስ ትንኮሳ እንዲያበቃ ለወራት ያካሄደውን ሰላማዊ ተቃውሞና አቤቱታ በአንክሮና በአድናቆት ስንከታተለው የቆየነው እውነታ ነው።
ይህን የህዝብ ሕጋዊ ጥያቄ ከማዳመጥና በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፣ ገዥው ቡድን በማንአለብኝነት በመነሳሳት ማህበረሰቡ የመረጣቸውን ወኪሎቹንና የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በማሰር የህዝቡን ብሶት አፍኖ እመቃውን ለመቀጠል ብዙ ጥሯል፤ የኃይል እርምጃዎችንም ሲወስድ ቆይታል።
አሁንም ያንኑ የጥፋት ጎዳና በመከተል የህዝቡን ጥያቄ በኃይል ለማፈን በከፋ ሁኔታ ጥረቱን ቀጥሏል። የመስጅድ ቦታዎችን እየደፈረ አማኞችን ከማሰር አልፎ ግድያ መፈጸም የተለመደ ተግባሮቹ እያደረገም ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) አገዛዙ እየወሰዳቸው ያሉትን ጸር-ሕዝብና ጸረ-ሀገር የጭቆናና የግፍ እርምጃዎችን በጥብቅ ያወግዛል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ሕብረተሰብ ለመብቱ መከበር በሚያደርገው ሰላማዊ ትግል ከጎኑ መቆማችንንና የትግል አጋርነታችንን ደግመን እየገለጽን አሁንም የሁሉም እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻቸው በህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት እየተደረገ ያለውን የመብት ነጠቃና እመቃ በጋራ እንዲከላከሉ እንጠይቃለን ።
የእምነት ነጻነት የሰብዓዊ መብት አካል ነው!
ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበት የሚደረገው ትግል ይቀጥላል!

No comments:

Post a Comment